በበጀት ዓመቱ የ535 ኪሎ ሜትር የአዳዲስ መንገዶች ግንባታ ተከናውኗል - ኢዜአ አማርኛ
በበጀት ዓመቱ የ535 ኪሎ ሜትር የአዳዲስ መንገዶች ግንባታ ተከናውኗል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2017 (ኢዜአ)፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የ535 ኪሎ ሜትር የአዳዲስ እና የፍጥነት መንገዶች ግንባታ መከናወኑን የኢትዮጵያ መንገዶች አሥተዳደር አስታወቀ።
በተጠናቀቀው በጀት አመት በመንገድ ግንባታ ዘርፍ ስኬታማ ተግባራት እንደተከናወኑም ተገልጿል።
የአሥተዳደሩ የኮሙኒኬሽን ቡድን መሪና የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ተወካይ አሥራት አሳሌ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ተግባራዊ በተደረጉ ስድስት የመንገድ ዘርፍ ልማት ፕሮግራሞች በመደበኛ የአስፋልት፣ የፍጥነት እና የጠጠር መንገድ ግንባታዎች ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
ለሀገሪቱ የመንገድ አውታር መስፋፋት የወረዳ መንገዶች ግንባታ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከታቸውን ነው የገለጹት።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በሀገሪቱ 535 ኪሎ ሜትር የአዳዲስ መንገዶች ግንባታና የፍጥነት መንገድ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም 339 ኪሎ ሜትር የነባር መንገዶች ማጠናከርና ደረጃ ማሻሻል ሥራ ተከናውኗል ብለዋል።
በከባድ፣ በመደበኛ እና በወቅታዊ 11 ሺህ 831 ኪሎ ሜትር የጥገና ሥራዎች በበጀት ዓመቱ መከናወኑን ጠቅሰዋል።
እንዲሁም 125 የአዲስ ድልድዮች ግንባታ እና የ83 ነባር ድልድዮች ጥገና መከናወኑንም ነው የተናገሩት።
በበጀት አመቱ ለተከናወኑ የመንገድ ልማት ሥራዎች 94 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ወጪ መደረጉን አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል በያዝነው የበጀት ዓመት ለሚከናወኑ 351 ፕሮጀክቶች 89 ነጥብ 13 ቢሊየን ብር መመደቡን ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ በ2018 የበጀት ዓመት 1 ሺህ 256 ነጥብ 3 ኪሎ ሜትር የመንገድ ግንባታ እና የከባድ ጥገና ሥራዎች እንደሚከናወኑም እንዲሁ።
በተጨማሪም በመንገድ ፈንድ አማካኝነት 15 ሺህ 645 ኪሎ ሜትር ወቅታዊ እና መደበኛ የጥገና ሥራዎች እንደሚሰሩም አመላክተዋል።