በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገትን እውን ለማድረግ በምክክር የሚገኝ መፍትሄ ወሳኝ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገትን እውን ለማድረግ በምክክር የሚገኝ መፍትሄ ወሳኝ ነው

ደሴ ፤ ነሐሴ 16/2017(ኢዜአ)፡- በኢትዮጵያ ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማረጋገጥ ሁለንተናዊ እድገትን እውን ለማድረግ በምክክር የሚገኝ መፍትሄ ወሳኝ መሆኑን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማሪያም አመለከቱ።
የምክክር ኮሚሽኑ "የሴቶች ተሳትፎና ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር" በሚል መሪ ሀሳብ በምስራቅ አማራ ከሚገኙ ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች ሴቶች ጋር ውይይት እያካሄደ ነው።
ኮሚሽነሩ በምክክሩ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ጠንካራ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን በማረጋገጥ ሁለንተናዊ እድገትን እውን ለማድረግ በምክክር የሚገኝ መፍትሄ ወሳኝ ነው።
የዘመናት ውስብስብ ችግሮቻችን ወደ ግጭት፣ ሁከትና ብጥብጥ እያመሩን በመሆኑ በምክክር ለይተን መፍትሄ ለመስጠት የሴቶች ተሳትፎና ሚና ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ሴቶች የእናትነት፣ የእህትነትና የሚስትነት ኃላፊነታቸውን እንዲሁም ጥበባቸውንና ብልሃታቸውን ተጠቅመው ለምክክሩ ውጤታማነት የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ኮሚሽኑ እያካሄደ ባለው ምክክር ለችግሮች እልባት በመስጠት ኢትዮጵያ እንድታሸነፍ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
የአጀንዳ ማሰባሰብና ተሳታፊዎችን የመለየት ስራ በአብዛኛው መከናወኑን ጠቁመው የልየታ ስራው ባልተሰራባቸው ውስን አካባቢዎችም በቀጣይ ለማከናወን እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለውጤታማነቱ ሴቶች ሚናቸውን እንዲወጡ በየደረጃው ውይይት እየተካሄደ ነው ያሉት ኮሚሽነሩ የዛሬው በክልሉ ደሴ ቀጠና የሚገኙ ሴቶችን ያሳተፈው ውይይትም ሚናቸውን ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሴቶች ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር ገነት ስዩም በበኩላቸው ለምክክር ኮሚሽኑ ተግባር ውጤታማነት ሴቶች የድርሻቸውን መወጣት እንዲችሉ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊና የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ፀሐይ ወርቁ በሰጡት አስተያየት የምክክሩን ዓላማ በማሳካት የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት በማረጋገጥ ረገድ የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።
ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን የመጡት ተሳታፊ ወይዘሮ በርነሽ ታደሰ በበኩላቸው የተጀመረው ምክክር ዳር ደርሶ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።
በውይይቱ ላይ ከደቡብ፣ ሰሜን ወሎና ሰሜን ሸዋ ዞኖች፣ ከኦሮሞና ዋግ ኽምራ ብሔረሰብ እንዲሁም ከደሴ፣ ኮምቦልቻ፣ ወልዲያና ደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደሮች የመጡ ሴቶች እየተሳተፉ ነው።