በአካባቢያችን የተዋቀረው የቀበሌ አደረጃጀት በአስተዳደር እና በልማት ስራዎች የቅርብ እገዛ እያደረገልን ነው -- የምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
በአካባቢያችን የተዋቀረው የቀበሌ አደረጃጀት በአስተዳደር እና በልማት ስራዎች የቅርብ እገዛ እያደረገልን ነው -- የምዕራብ ሸዋ ዞን ነዋሪዎች

አምቦ፤ ነሐሴ 16/2017(ኢዜአ)፡- በአካባቢያቸው የተዋቀረው የቀበሌ አደረጃጀት በአስተዳደር እና በልማት ስራዎች የቅርብ እገዛ እያደረገላቸው መሆኑን የምዕራብ ሸዋ ዞን ዳኖ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ።
ኢዜአ ያነጋገራቸው በምዕራብ ሸዋ ዞን በዳኖ ወረዳ የዳኖ ሸነኒ ቀበሌ ነዋሪዎች እንዳሉት፥ አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት በአስተዳደር እና በልማት ስራዎች እያገዛቸው ነው።
በወረዳው የዳኖ ሸነኒ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጀማል ጅብሪል፤ በአካባቢያቸው በአዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት የሚፈልጉትን የመንግስት አገልግሎት በቅርበት እና በአንድ ቦታ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
ይህም ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበታቸውን መቆጠብ በመቻሉ ትኩረታቸው የልማት ስራ ላይ እንዲሆን እድል መፍጠሩን ጠቅሰው በአስተዳደሩ አማካኝነት የልማት ስራቸውን ለማሳደግ የሚያግዙ ግብዓቶችን በአግባቡ እያገኙ መሆኑንም አውስተዋል።
የቀበሌ አደረጃጀቱ በተለይም ህዝቡና የጸጥታ አካሉ ተቀናጅተው በአካባቢው የተገኘውን ሰላም ዘላቂ ለማድረግ እገዛ ማደረጉንም ተናግረዋል።
ሌላው የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ገመቹ አማና በበኩላቸው፣ ከዚህ በፊት አገልግሎት ለማግኘት ወደ ወረዳ በመሄድ ለተለያየ ወጪ ይጋለጡ እንደነበር አስታውሰዋል።
ከአንድ ዓመት ወዲህ ግን በአካባቢው የቀበሌ አስተዳደር መዋቅር በመዘርጋቱ የመሰረተ ልማት ጥያቄዎቻቸው ምላሽ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።
አዲሱ የቀበሌ አስተዳደር መንግስታዊ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ እና በቅርበት ማገኘታቸው ገልጸው ለዚህም መንግስት ሊመሰገን ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አቶ ፋዬራ አዱኛ ናቸው፡፡
በዞኑ የዳኖ ሸነኒ ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ ግርማ ለማ፤ አደረጃጀቱ የሕብረተሰቡን አኗኗር ለመቀየርና የልማት ጥያቄያቸው ፈጣን ምላሽ እንዲያገኝ ዓላማ አድርጎ መቋቋውን አታውሰዋል።
አዲሱ የቀበሌ አደረጃጀት ከተዘረጋ በኋላም የህዝቡን የአገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽ እና ቀልጣፋ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጎን ለጎን የህዝቡ የልማት ጥያቄዎች ፈጣን ምላሽ እንዲያገኙ በተለይም ከግብርና ግብዓት አቅርቦት አንጻር ውጤታማ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።