በሥራ ፈጠራ የስኬት ጉዞ የጀመረው ወጣት ተሞክሮ - ኢዜአ አማርኛ
በሥራ ፈጠራ የስኬት ጉዞ የጀመረው ወጣት ተሞክሮ

(በያንተስራ ወጋየሁ - ከዲላ ኢዜአ ቅርንጫፍ)
አንዳንዴ መዳረሻን የሚያሳምረው መነሻችን ነው ሲባል ይደመጣል።መነሻው ጥሩ ከሆነ ኋላ ለሚገኘው ስኬት መደላድል ይሆናል ለማለት ነው። ነገን አርቆ በማሰብና በማለም መስራት የህይወት ጉዞን ቀናና ስኬታማ ለማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው። የሚገጥም ፈተናን እያሰቡ ወደኋላ ከማለት ይልቅ መፍትሄ በመፈለግ ወደስራ የገቡ ስኬት ሲያስመዘግቡ ይታያሉ። በዚህም ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎችም ወጣቶች ሲተርፉ ይስተዋላል።
በፈተና ወደኋላ ሳይል ከችግሩ የሚወጣበትን መንገድ በመፈለግ ስኬት ማስመዝገብ የጀመረው የወናጎ ከተማ ወጣት ኤፍሬም ጴጥሮስ ለእዚህ አንድ ማሳያ ነው።
ወጣቱ በከተማው የቱቱፈላ ቀበሌ ነዋሪ ነው። በ2015 ዓ.ም በ12ኛ ክፍል አገር አቀፍ ፈተና ያመጣው ውጤት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የሚያስገባ አልነበረም። በዚህ ምክንያት ሁለት ዓመታተን እንዲሁ ያለስራ አባክኗል። ያለሥራና ያለትምህርት ባሳለፋቸው ሁለት ዓመታት ድብርት ውስጥ ገብቶ እንደነበር ያስታወሰው ወጣት ኤፍሬም በዚህ ሁኔታ ግን ህይወቱን መቀጠል አልፈለገም።
በዙሪያው ለሀብት ምንጭ የሚሆኑ ነገሮችን ትኩረት ሰጥቶ ማሰላሰል ጀመረ። በወናጎ ከተማ ራሱን ከመለወጥ ባለፈ የአካባቢውን ማህበረሰብ መጥቀም የሚችልባቸውን የሥራ አማራጮችን ማየቱን ቀጠለ። በዚህ ወቅት ነበር በአዲስ እሳቤ የተጀመረውና ብዙዎች በስፋት በመሳተፍ ተጠቃሚ እየሆኑበት ያለው የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ቀልቡን የገዛው።
ይህ ሀገራዊ ኢንሼቲቭ ማህበረሰቡ ያለውን ልምድ የበለጠ በማስፋትና በማዘመን ተጠቃሚ እያደረገው በመምጣቱ የእሱንም ችግር ሊፈታ እንደሚችል ወጣቱ በማመኑ ቀዳሚ ትኩረት ያደረገው የዶሮ እርባታ ሥራ ላይ ነው።
መንግስት ለማህበረሰቡ የዶሮ ጫጩቶችን በብዛት ማሰራጨት ተከትሎ ብዙች በዶሮ እርባታ ሥራ ተሰማርተዋል። የወናጎ ከተማ ነዋሪዎችም በዘርፉ ለመሰማራት ባላቸው ከፍተኛ ፍላጎት የዶሮ ጫጩቶችን በብዛት ሲረከቡ በየዕለቱ ማየቱ በውስጡ አንድ ነገር አጫረበት። በከተማው ለብዙ ሰዎች ለዶሮ እርባታ የሚሆን በቂ ስፍራ ማግኘት አዳጋች መሆኑ ለአምራቾች ትልቅ ፈተና ነው። ይህን የተረዳው ወጣቱ ለዚህ ችግር መፍትሄ ሊሆን የሚችል ነገር ቢሰራ አንድም ለራሱ ሥራ መፍጠር ነው፤ በሌላ ቡኩል የነዋሪዎችን ችግር መፍታት መሆኑን አሰበ።
በአካባቢው ካሉ ግብአቶች በቀላል ወጪ ለማህብረሰቡ ይጠቅማል ያለውን ተንቀሳቃሽ የዶሮ ቤት ለመስራት ወሰነ። ጉዳዩን ከራሱና ከሌሎች ጋርም መከረበት። በእዚህም ወደስራው ለመግባት የሚያስችል ገንቢ ምክረ ሀሳብ አገኘ። ሀሳቡ አዲስና ለነዋሪውም የሚሰጠው ጥቅም የጎላ መሆኑ ደግሞ ይበልጥ አበረታታው። ይህም ተጨማሪ ብርታት ሆኖት ሀሳቡን ወደድርጊት በመቀየር "ተንቀሳቃሽ የዶሮ ቤት" በመስራት ለሽያጭ ማቅረብ ጀመረ።
ተንቀሳቃሽ የዶሮ ቤቱ በጥቂት ቦታ በአንድ ጊዜ 120 የዶሮ ጫጩቶችን ለማርባት የሚያስችልና ሰፊ ቦታ የማይዝ መሆኑም በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ እድርጎታል። ወጣት ኤፍሬም በወናጎ ከተማ ያለውን የቦታ ችግር ለመፍታት በአካባቢው ያለን ግብአት ተጠቅሞ የሰራው ተንቀሳቃሽ የዶሮ ቤት ዛሬ ከጌዴኦ ዞንና ወናጎ ከተማ ባለፈ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደረጃ በብዙዎች ዘንድ ተፈላጊ እየሆነ መጥቷል።
ከስኬቶቹ መካካል
በዚህ ሥራው በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ከመሆን ባለፈ ተስፋ ሰጪ ለውጥ እያሳየ ነው። የራሱን ሥራ ከፈጠረ ከአንድ ዓመት ያነሰ ጊዜ ቢሆነውም ከራሱና ከቤተሰቦቹ አልፎ ለሦስት የአካባቢው ወጣቶችም የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል። በወር ከአራት በላይ የተንቀሳቃሽ ዶሮ ቤቶችን በመሸጥ ከ100 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚያገኝ የሚናገረው ወጣቱ የዶሮ ቤት ሥራውም በህይወቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ለውጥ እንዲያመጣና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነቱን እንዳሳደገው ይናገራል።
በዚህም ሰርቶ ለመለወጥ ያለው ፍላጎት መነሳሳቱን የገለጸው ወጣቱ ጎን ለጎን የዶሮ እርባታ ሥራ ጀመረ። ተንቀሰቀሽ የዶሮ ቤት አዘገጅቶ ከመሸጥ ባለፈ ለሌሎች አርቢዎች ማስተማሪያ ይሆናል በሚል የ45 ቀን የእንቁላል ጣይ የዶሮ ጫጩቶችን በማርባት ለአካባቢ ማህበረሰብ እያቀረበ ይገኛል። ይህም ሥራውን በመጠንና በአይነት ለማስፋትና ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት አስችሎታል።
የለውጡ ምክንያት
"በአጭር ጊዜ ላሳየሁት ለውጥ ምክንያቱ ለሥራ ያለኝ ተነሳሽነት ነው" የሚለው ወጣቱ የተጠናከረ የገበያ ትስስርም እንዳለው ተናግሯል። በሚገጥም ችግር ተስፋ መቁረጥ መፍትሄ እንደማይሆን ለሌሎች ወጣቶች ይመክራል። ከዚያ ይልቅ በአካባቢ ያለን ሀብት ለልማት በማዋል ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መስራት እንደሚገባ ነው የገለጸው። በተለይ ኑሮ ለውጥ ለማምጣት በሀገራዊ ኢንሼቲቮች በመሳተፍ ተጠቃሚ ለመሆን ተግቶ መስራት ይገባል ባይ ነው።
የወጣቱን የዶሮ ቤት በመጠቀም በዶሮ እርባታ ሥራ ከተሰማሩ የወናጎ ከተማ ወጣቶች መካከል ወጣት አማኑኤል ቦጋለ አንዱ ነው። ተንቀሳቃሽ የዶሮ ቤቱ በውስን ስፍራ ዶሮ የማርባት ፍላጎቱን አሳክቶለታል። ሦስት ካሬ ብቻ የሚይዘውን የዶሮ ቤት በ20 ሺህ ብር በመግዛት በ120 የዶሮ ጫጩቶች ሥራውን ጀምሮ እያከናወነ ይገኛል። በአሁኑ ወቅትም ከራሱ ፍጆታ ባለፈ እንቁላል በመሸጥ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ነው የተናገረው። የዶሮ ቤቱ የመመገቢያ፣ የማደሪያና ኩስ መጥሪግያ በዘመናዊ መንገድ የተዘጋጀለት መሆኑ ስራውን በቀላሉ ለማከናውን እንዳስቻለውም ገልጿል።
የዶሮ ቤቱ እሱን ጨምሮ ለብዙዎች ከቦታ እጥረት ጋር በተያያዘ የነበረባቸውን ችግር እንደፈታ የገለጸው ወጣቱ፣ በሌማት ትሩፋት የተጀመረው የዶሮ እርባታ ሥራ ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ተናግሯል። ይህን የሌማት ትሩፋት ሥራ የሚያጠናክሩ የፈጠራ ሥራዎች ደግሞ ተጠቃሚነትን ይበልጥ ስለሚያሳድጉ መስፋፋት እንዳለባቸውም ነው የተናገረው።
በወናጎ ከተማ አስተዳደር ግብርና ዩኒት የእንስሳት ዘርፍ አስተባባሪ ወይዘሮ ፀደይ አጋደ በከተማዋ ከፍተኛ የሰዎች ጥግግት እንዳለ ያነሳሉ። ይሁን እንጂ የአካባቢውን ሀብቶች በመጠቀም ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወኑ ስራዎች ብዙዎች ተጠቃሚ እየሆኑና ህይወታቸውን እየለወጡ መጥተዋል። ነዋሪውም በዶሮ እርባታ ተሰማርቶ ተጠቃሚ ለመሆን ያለው ፍላጎት ከፍተኛ ነው።
የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭን ተከትሎ በዶሮ እርባታ የሚሰማሩ ሰዎች ቁጥር ቢጨምርም የቦታ እጥረት ፈተና ሆኖ መቆየቱን ያነሳሉ። የህብረተሰቡን የቦታ ጥያቄ መፍታት ለአስተዳደሩ መሰረታዊ ተግዳሮት እንደነበር አስታውሰው፤ ወጣት ኤፍሬም በአካባቢ ከሚገኝ ግብዓት ተንቀሳቃሽ የዶሮ ቤት ስርቶ ለሽያጭ ማቅረቡ ችግሩን እያቀለለው መሆኑን ይናገራሉ።
ወይዘሮ ፀደይ እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በከተመው በሦስት የዶሮ መንድሮች የዶሮ እርባታ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል። በዚህም 14 በማህበር የተደራጁ እና ከ80 በላይ በግል የተሰማሩ ዶሮ አርቢዎች በመሳተፍ ላይ ናቸው። የልማት ሥራው እንቁላልና ዶሮ ለማህበረሰቡ በተመጣጣኝ ዋጋ እያስቻለ ነው። በወጣቱ የተሰራው ተንቀሳቃሽ የዶሮ ቤትም ከቦታ ጥበት ጋር በተያያዘ ከነዋሪዎች ሲነሳ የነበረውን ጥያቄ እየፈታ መሆኑን አስተባባሪዋ ይገልጻሉ። እንደወጣት ኤፍሬም የዜጎችን ችግር የሚፈቱና በመንግስት የሚከናወኑ የልማት ተግባራትን የሚያግዙ ፈጠራ የታከለባቸው ሥራዎች ልማቱ የበለጠ ስለሚያጠናክሩ የሚደገፉና የሚበረታቱ መሆናቸውን ነው የገለጹት።
በየአካባቢው ያልተነኩ ሀብቶች አሉ። ዋናው ነገር ግን እነዚህን ሀብቶች እንዴት ወድልማት በመቀየር ተጠቃሚ መሆን ይቻላል የሚለው ነው። በተለይ ወጣቶች ሥራ የለም በሚል ምክንያት የማይተካ ጊዜን ያለአግባብ ማሳለፍ አይገባም። ህገወጥ ስደትን ምርጫ ማድረግም አግባብ እንዳልሆነ የወጣት ኤፍሬም ተሞክሮ እንድ ማሳያ ነው።
መንግስት የዜጎችን ተሳትፎና ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የተለያዩ ኢኒሸቲቮችን ቀርጾ ወደተግባር አስገብቷል። በእነዚህ ኢኒሼቲቮች መሳተፍና እንዴት ስኬታማ መሆን እንደሚችሉ ቆም ብሎ ማሰብ ብቻ ነው ከእነሱ የሚጠበቀው። ያኔ መዳረሻቸውን አርቀው ማለም ይጀምራሉ። መነሻቸው መሰረት ከያዘ መዳረሻቸውን ማሳመር ይችላሉና ከወናጎ ከተማ ወጣት ኤፍሬም የስኬት ጉዞ ትምህርት መውሰድ ይገባል።