ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ ለግድቡ ግንባታ ያሳየው ተሳትፎ የኢትዮጵያዊያንን ቁጭት እና አይበገሬነት በተግባር ያሳየ ነው

አሶሳ፤ነሐሴ 16/2017 (ኢዜአ)፦ ህብረተሰቡ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ያሳየው ተሳትፎ የኢትዮጵያዊያንን ቁጭት እና አይበገሬነት በተግባር ያሳየ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።

በኢትዮጵያውያን ገንዘብና ጉልበት ተገንበቶ በመገባደድ ላይ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የስኬት ማሳያና የድል ምልክትም ተደርጎ የሚቀመጥ ቋሚ ቅርስ ነው።

የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ የተሟላ ብርሃን ከመስጠትም ባለፈ አዲስ የተፈጥሮ ምህዳር በመፍጠር፣ ዓሳ እየተመረተበት፣ ለመዝናኛነት ከሚመረጡ ድንቅ ስፍራዎች መካከል የሚሆን ነው።

የግድቡ መገንባት በተለይም ለቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልና አካባቢው ልዩ የመስህብ ስፍራና በቱሪዝም ዘርፍ የገቢ ምንጭ በመሆን የሚያገለግል ይሆናል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች የህዳሴ ግድብ የአሁኑ ትውልድ የሚኮራበት ሃብትና የመጪው ትውልድ ቅርስ ስለመሆኑ ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሰኢድ ሙሐመድ፤ ግድቡ የኢትዮጵያዊያንን የመቻልና የመፈፀም አቅም ያረጋገጠ፤ በአንድ ልብ ከዳር ዳር በመሰባሰብ በገንዘብና በጉልበት ሁሉም የተሳተፈበት የጋራ ኩራታችን ነው ብለዋል።

ከብዙ ውጣ ውረድ፣ የውስጥ ፈተናዎችንና የውጭ ጫናዎችን አልፎ ለስኬት በመብቃቱ ሂደት የህዝቡ ያልተቋረጠ ድጋፍ በተለይም የመንግስት በሳል አመራርና ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑንም አንስተዋል።

ሌላ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ አልሃረም ሙሀመድ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን ኩራት የወደፊቷ ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሀገር ሀብት ከመሆኑ ባሻገር የኢትዮጵያዊያን ጥንካሬ እና ቁጭትን ያስመሰከረ ፕሮጀክት ነው ያሉት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ከፋለ አደመ ናቸው።

ለግድቡ ዘላቂ ደህንነት በአረንጓዴ አሻራ እና ሌሎች ዘርፎች የሁላችንም ትብብርና ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም