የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሰሜን አሜሪካ እና ካናዳ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተወካዮች ምርጫ በቅርቡ ያካሂዳል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 16/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በሰሜን አሜሪካ እና ካናዳ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተወካዮች ምርጫን በቅርቡ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ገለጸ።

ኮሚሽኑ እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራትን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥቷል።

የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ቃል አቀባይ ጥበቡ ታደሰ በሰጡት መግለጫ፥ ኮሚሽኑ አካታችነትና አሳታፊነቱን በተግባር እያረጋገጠ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በዚህም ከሀገር ውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ተቋማት እና ማህበራትን በማሣተፍ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ እና በካናዳ የአጀንዳ ማሰባሰብና የተወካዮች ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህ ሂደትም ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያን፣ ተቋማት እና ማህበራት እንደሚሳተፉ ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ ዳያስፖራ ወገኖችን በአካል እና በበይነ መረብ እንዲሳተፉ ሁኔታዎችን እንደሚያመቻችም ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅትም ለመሰብሰቢያ አዳራሽ እና ለሎጂስቲክስ ዝግጅት ይመች ዘንድ የምዝገባ ሂደት እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

በሰሜን አሜሪካ የሚካሄደው የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተወካዮች ምርጫ ነሐሴ 24 ቀን 2017 ዓ.ም እንደሚከናወን ጠቁመው፤ የካናዳውም የሰሜን አሜሪካውን ተከትሎ እንደሚካሄድ አስታውቀዋል።

ሂደቱ ውጤታማ እንዲሆንም ሁሉም አካላት የነቃ ተሣትፎ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በህግ-ጥላ ስር የሚገኙ ዜጎችን በሀገራዊ ምክክሩ ለማሣተፍ ከፍትህ ሚኒስቴር እና ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር በጎ ምላሽ ተገኝቶ ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ኮሚሽኑ በደቡብ አፍሪካ ያካሄደው የምክክር ሂደት በሁሉም መስኩ ውጤታማ እንደነበር አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም