በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ተኪ ምርቶች ተመርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ተኪ ምርቶች ተመርተዋል

ወላይታ ሶዶ፤ነሐሴ 16/2017 (ኢዜአ):-በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ተኪ ምርቶች መመረታቸውን የክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ አስታወቀ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተለይም በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ የነበረውን እንቅስቃሴና የተገኘውን ውጤት በተመለከተ የክልሉ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ቦጋለ ቦሼ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
በማብራሪያቸውም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተለያዩ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በብዛትና በጥራት በማምረት ለገበያ ማቅረብ መቻሉን አንስተዋል።
በተለይም ምግብና የጨርቃጨርቅ ምርቶች፣ የሳሙና ምርቶች፣ የእንጨትና ብረታ ብረት እንዲሁም ሌሎችም መመረታቸውን ዘርዝረዋል።
በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በድምሩ ከ2 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ተኪ ምርቶች መመረታቸውን ኃላፊው ገልጸዋል።
የታየው አፈፃፀም የውጭ ምንዛሪ ወጪን በመቀነስ ትርጉም ያለው ውጤት ያመጣ መሆኑን ተናግረው፥ በክልሉ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ከፍተኛ መነቃቃትና ማንሰራራት እየታየ መሆኑን አንስተዋል።
በክልሉ ባለፉት ሁለት ዓመታት 2 ሺህ 400 ነባር መካከለኛ እና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎችን ማሳደግ መቻሉንና በከፍተኛ ኢንዱስትሪ ዘርፍ የተሰማሩትም ከ230 ወደ 390 ማድረስ ተችሏል ብለዋል።
የመስሪያና መሸጫ ቦታን ማመቻቸት ጨምሮ ሌሎች ቀልጣፋ አሰራሮች ተዘርግተው ዘርፉን የማነቃቃት ስራ መከናወኑንና አሁንም ተጠናክሮ መቀጠሉን አረጋግጠዋል።
የመነሻ ካፒታል፣ የማምረቻ እና የመሸጫ ቦታ ከማቅረብ ጀምሮ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አንስተው፥ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ገልጸዋል።
በወላይታ ሶዶ ከተማ "ብቁ የቤትና የቢሮ ዕቃ ማምረቻ እና መሸጫ ኢንተርፕራይዝ" ስራ አስኪያጅ አቶ ብሩክ ሎሃ፤ የእንጨት ውጤቶች በማምረት ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸወን ተናግረዋል።
የገበያ ትስስሩና የሀገር ውስጥ ምርት ለመግዛት ያለው ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን አንስተው፥ ለብዙዎች የስራ እድል መፍጠራቸውንም ገልጸዋል።