"ለመንገዴ" የሞባይል መተግበሪያ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት የሚያገኙ ዜጎችን ክብርና ደህንነት መጠበቅ ያስችላል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2017(ኢዜአ)፦ "ለመንገዴ" የሞባይል መተግበሪያ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት የሚያገኙ ዜጎችን ክብርና ደህንነት መጠበቅ የሚያስችል መረጃ የሚሰጥ መሆኑን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር እና በዓለም አቀፍ ሥራ ድርጅት ትብብር የበለጸገው ''ለመንገዴ'' የሞባይል መተግበሪያ ይፉ ሆኗል።


 

የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ነቢሃ መሐመድ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት የሚያገኙ ዜጎችን ክብርና ደህንነት ማስጠበቅ የሚያስችሉ አሰራሮች ገቢራዊ እየተደረጉ ነው፡፡

በኢትዮጵያውያን የበለጸገው "ለመንገዴ" የሞባይል መተግበሪያ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪትን በማዘመን ዜጎች ከቅድመ ጉዞ ዝግጅት ጀምሮ በመዳረሻ ሀገራት እንግልት እንዳይገጥማቸው ጠቃሚ መረጃ የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሥራ ስምሪት የሚወስዱ ዜጎችን መብትና ግዴታ፣ የአሰሪና ሰራተኛን የሥራ ግንኙነት እንዲሁም ከውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ሲመለሱ በሀገራቸው የራሳቸውን ሥራ መጀመር እንዲችሉ ግንዛቤ ያስጨብጣል ብለዋል፡፡

የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች የማሰልጠኛ ተቋማትን፣ ምርመራ የሚሰጥባቸው የጤና ማዕከላትን፣ የሥራ ስምሪት መዳራሻ ሀገራትን የኢትዮጵያ ኤምባሲና ቆንስል ቢሮዎች አድራሻ የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በዚህም ዜጎች በውጭ ሀገራት የሥራ ስምሪት ወቅት ችግር ቢገጥማቸው ለሚመለከተው አካል ጥቆማ መስጠት ያስችላቸዋል፤ የዜጎችን መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚደረገው ጥረትም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡

የዓለም ሥራ ድርጅት የኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ዳይሬክተር ኩምቡላ ንዳባ በበኩላቸው፤ የውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ለሚያገኙ ኢትዮጵያውያን ጥበቃና ደህንነት ወሳኝ መሆኑ አንስተዋል፡፡

"ለመንገዴ" የሞባይል መተግበሪያ የኢትዮጵያና የዓለም ሥራ ድርጅትን የጋራ ጥረት የሚያንጸባርቅ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ፣ በዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና በማህበራዊ አጋሮች መካከል ያለው ትብብር አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቴክኖሎጂ የታገዘ የሥራ ስምሪት ለዜጎች ደህንነት ወሳኝ መሆኑን በመግለጽ፤ ኢትዮጵያ መሰል የቴክኖሎጂ ስራዎችን ጥቅም ላይ ለማዋል የምታደርገውን ጥረት እንደግፋለን ብለዋል፡፡

"ለመንገዴ"ን አገልግሎት በቴሌ ብር መተግበሪያ ላይ ማግኘት እንደሚቻል ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም