የወተት ምርትን ጥራትና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተከናወኑ ነው - ባለስልጣኑ - ኢዜአ አማርኛ
የወተት ምርትን ጥራትና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተከናወኑ ነው - ባለስልጣኑ
አዳማ፤ ነሐሴ 15/2017 (ኢዜአ)፡- የወተት ምርትን ጥራትና ደህንነትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ ስራዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን ኤስ.ኤን.ቪ ኢትዮጵያ ከተሰኘ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር የወተት ምርት ጥራትና ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በአዳማ አካሂዷል።
በባለሥልጣኑ የእንስሳት ምርት ሬጉላቶሪ መሪ ሥራ አስፈጻሚ አያሌው ሹመት (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደናገሩት የኢትዮጵያ ግብርና ባለሥልጣን በግብርናው ዘርፍ የተጠናከረ የምርት ጥራት ቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት እየሰራ ነው።
በተለይም የወተት ምርት ጥራትና ደህንነት በማስጠበቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።
የወተት አምራቾችን መከታተልና መቆጣጠር አንዱ የባለስልጣኑ ተግባር በመሆኑ በአመራር ሂደት የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት እንዲስተካከሉ ለማድረግ ግንዛቤ እየተፈጠረ መሆኑን አስረድተዋል።
''በሀገራችን የወተት ኢንዱስትሪው ገና በማደግ ላይ ነው'' ያሉት መሪ ሥራ አስፈጻሚው፤ ከወተት ምርት ጥራትና ደህንነት ጋር ተያይዞ ያሉትን ክፍተቶች በመሙላት ዘርፉ እንዲያድግ እንደሚሰራም አመልክተዋል።
ህብረተሰቡ ጥራትና ድህንነቱ የተጠበቀ የወተት ምርት እንዲያገኝ ባለስልጣኑ የቁጥጥር ስራዎችን እንደሚያጠናክር አስታውቀዋል።
በመሆኑም በሁሉም የወተት እሴት ሰንሰለት ላይ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት በአግባቡ ሚናቸውን መወጣት እንዲችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱን ገልጸዋል።
በባለሥልጣኑ የወተትና ማር ምርቶች ሬጉላቶሪ ዴስክ ኃላፊ ስምኦን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሻሻል ከመስራት ጎን ለጎን የወተት ጥራትና ደህንነት ማስጠበቅም ትኩረት ተሰጥቶታል።
የወተት ምርት ጥራትና ደህንነት ለማስጠበቅ ለመጀመሪያ ጊዜ በወተት ልማት የተሰማሩ 71 አምራቾች ላይ ከምርት ደህንነትና ጥራት አኳያ ጥናት መካሄዱን ጠቁመው በጥናቱም የጥራት ጉድለት እንዳለ መረጋገጡን ተናግረዋል።
በግኝቱ መሠረት የማሻሻያ እርምጃዎች እንዲወስዱ መደረጉንና ባለስልጣኑም ቀጣይነት ያለው ክትትልና ቁጥጥር አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል በሲዳማ ክልል ወንዶ ገነት ወረዳ በተሻሻሉ የወተት ላሞች እርባታ የተሰማሩት አቶ ሰንበቶ ሙሉ በሰጡት አስተያየት የወተት ምርትና ጥራት ለማስጠበቅ ከመኖ አቅርቦት አንስቶ ወተቱ የሚታለብበት ዕቃ፤ የወተት ምርት የሚቀመጥበት ሁኔታ እና የሚጓጓዝበት መንገድ በጥንቃቄ እንደሚያከናወኑ ተናግረዋል።
ለወተት ምርትና ምርታማነት ትኩረት የሚሰጠውን ያህል ለጥራትና ደህንነትም ትኩረት ሰጥቶ መሰራት በዘላቂነት ተጠቃሚ እንደሚያደርግም አስረድተው፤በቀን 180 ሊትር የወተት ምርት በማምረትና ለአካባቢው ገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን አመላክተዋል።