ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ኃብትን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለመከላከል በቅንጅት እየሰራች ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2017 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በወንጀል ድርጊት የተገኘ ኃብትን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለመከላከል አገራዊ አቅምን በመፍጠር ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራች መሆኑን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ገለጸ፡፡

ኢትዮጵያ ከነሐሴ 16 እስከ 24 ቀን 2017 ዓ.ም ድረስ የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የህገ-ወጥ ገንዘብ ዝውውር ወንጀልን መከላከል ቡድን ዓመታዊ ጉባዔን ታስተናግዳለች።

ጉባዔውን በማስመልከት የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ለመገናኛ ብዙኃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሙሉቀን አማረ በመግለጫቸው፤ በኢትዮጵያ ጉባዔውን ማስተናገድ የሚያስቸል በቂ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

በጉባኤው ከ21 አባል ሀገራት የተውጣጡ የፋይናንስ ደህንነት ተቋማት፣ አንድ ታዛቢ ሀገር እንዲሁም የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር ከ2013 ጀምሮ አባል በመሆን እየተሳተፈች መሆኑን ጠቁመው፤ ወንጀሎቹን ከመከላከል እና ከመቆጣጠር አንጻርም አገራዊ አቅምን በማሳደግ ከመሰል ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራች መሆኑን ጠቅሰዋል።

ቡድኑ 25ኛው የሚኒስትሮች ምክር ቤትና 50ኛው የከፍተኛ ባለሙያዎች ግብረ ኃይል ስብሰባ እንዲሁም 8ኛው የመንግስት እና የግል ዘርፍ ተቋማት ምልዓተ ጉባኤ እንደሚያካሄድም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ወንጀሉን ለመከላከል የፖለቲካ ቁርጠኝነት በመውሰድ እየሰራች መሆኑን ጠቁመው፤ ለዚህም ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁማ እንቅስቃሴ እያደረገች እንደምትገኝ አመልክተዋል።

በወንጀል ድርጊት የተገኘ ኃብትን ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎች ድንበር ተሻጋሪ እንደሆኑና የሚያስከትሉት ተጽዕኖ ዓለም አቀፍ መሆኑን ተናግረዋል።

ጉባዔው ቀጣናዊ ትብብርን ለማጠናክርና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ከማገዙ ባሻገር ምክረ ሀሳቦች የሚቀርቡበት መሆኑን አመላክተዋል።

ጉባዔው አለም አቀፋዊ ትብብር እና ቅንጅትን ለማጠናከር ጉልህ ሚና እንዳለውም ጠቁመዋል።

በወንጀል ድርጊት የተገኘ ሃብትን ህጋዊ ማስመሰል እና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀሎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሚደረገው ጥረት ተጨማሪ አቅም የሚፈጠርበት መሆኑን አንስተዋል።

ከነሐሴ 16 እስከ 24 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ በሚካሄደው ጉባኤ ከ1ሺህ 150 በላይ ታዳሚዎች ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የህገ-ወጥ ገንዘብ ዝውውር ወንጀልን መከላከል ቡድን ተቋም በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አስመስሎ የማቅረብ፣ ሽብርተኝነትንና የጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች ብዜትን በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎችን ለመከታተል እና ለመቆጣጠር አለም አቀፍ ህጎች ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲተገበሩ ታልሞ የተቋቋመ ሲሆን ኢትዮጵያ የወቅቱ ፕሬዝዳንት ሆና እያገለገለች ትገኛለች።

የምስራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ የህገ-ወጥ ገንዘብ ዝውውር ወንጀል መከላከል ቡድን እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1999 የተቋቋመ ሲሆን ዋና መቀመጫውንም በታንዛኒያ መዲና ዳሬሰላም ያደረገ ነው፡፡

የቡድኑ አባል ሀገራትም አንጎላ፣ ቦትስዋና፣ ኢትዮጵያ፣ ቡሩንዲ፣ ኤርትራ፣ ኢስዋቲኒ፣ ኬንያ፣ ሌሶቶ፣ ማዳጋስካር፣ ማላዊ፣ ሞሪሸስ፣ ሞዛምቢክ፣ ናሚቢያ፣ ሩዋንዳ፣ ሲሼልስ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ፣ ዛምቢያ እና ዚምባብዌ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም