ቀጥታ፡

ጉባኤው በአባል ሀገራት መካከል ጠንካራና ተዓማኒነት ያለው የትምህርት ምዘና ስርዓት መገንባት የሚያስችል ልምድ የሚቀሰምበት ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2017 (ኢዜአ)፡- የአፍሪካ የትምህርት ምዘና ማሕበር ጉባኤ በአባል ሀገራት መካከል ጠንካራና ተዓማኒነት ያለው የትምህርት ምዘና ስርዓት መገንባት የሚያስችል ልምድ የሚቀሰምበት ነው ሲሉ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ገለጹ።

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት 41ኛውን የአፍሪካ ትምህርት ምዘና ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።

"የትምህርት ምዘናን ለማሸጋገር ጥራት ያለው ትምህርትና በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄደው 41ኛው የአፍሪካ ትምህርት ምዘና ማህበር ዓመታዊ ጉባኤ ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት በስካይ ላይት ሆቴል ይካሄዳል።

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር እሸቱ ከበደ (ዶ/ር) ጉባኤውን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ከአፍሪካ የትምህርት ምዘና ማህበር ጋር ተቀራርበን በመስራታችን መድረኩን እንድናዘጋጅ ተመርጠናል ብለዋል።

በመጭው ቅዳሜና እሁድ ቅድመ ጉባኤ የሚደረግበት መርሀ ግብር እንዳለም ተናግረዋል።

ጉባኤው በአባል ሀገራት መካከል ጠንካራና ተዓማኒነት ያለው የትምህርት ምዘና ስርዓት መገንባት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም በትምህርትና ምዘና ስርዓት ዙሪያ ያሉ እሳቤዎች፣ ቴክኖሎጂዎች፣ ልምዶችና ተሞክሮዎች እንደሚቀርቡም ተናግረዋል።

በዘርፉ ፍትሀዊ አሰራርን ለማስፈን የሚያስችል ምቹ ቀጣናዊና አህጉራዊ ትስስር ለመፍጠር የሚመከርበት መድረክ መሆኑን ገልጸዋል።

በምዘናና ፈተና ዓለም አቀፍ ተሳትፎን ማሳደግ፣ በምርምር የታገዘ የትምህርትና ምዘና ስርዓት ማንበር፣ ዘላቂ ትብብር መፍጠር፣ በጋራ መስራት የጉባኤው የትኩረት መስኮች መሆናቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያን በትምህርትና ምዘና ስርዓት ልምዷን የምታካፍልበት መድረክ እንደሚኖር ጠቅሰው ጉባኤው ለአፍሪካ የትምህርት ስርዓት መሻሻል የጎላ አበርክቶ እንዳለውም አንስተዋል።

ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ በተለያዩ ዘርፎች ያከናወነቻቸውን የልማት ስራዎች የምታሳይበት መርሀ ግብር መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡

በጉባኤው ላይ ከሰላሳ በላይ ሀገራት የሚመጡ አምስት መቶ የልዑካን ቡድን አባላት የሚሳተፉ ሲሆን 124 የተመረጡ የምርምር ወረቀቶች ይቀርባሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም