በዞኑ የሰፈነው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን የህዝቡ እና የጸጥታ አካላት ጥምረት ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ የሰፈነው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን የህዝቡ እና የጸጥታ አካላት ጥምረት ተጠናክሮ ቀጥሏል

ነቀምቴ ፤ነሐሴ 15/2017(ኢዜአ)፡- በምስራቅ ወለጋ ዞን የሰፈነው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን የህዝቡ እና የጸጥታ አካላት ጥምረት ተጠናክሮ መቀጠሉ ተገለጸ።
''ሰላም የልማት እና ብልጽግና መሰረት ነው'' በሚል መሪ ሀሳብ በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የተሳተፉበት የሰላም ኮንፍረንስ እየተካሄደ ነው።
በዞኑ በጉቶ ጊዳ ወረዳ በተካሄደው ውይይት ላይ የተሳተፉ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት በዞኑ ባለፉት ዓመታት አጋጥሞ በነበረው የጸጥታ ችግር ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለው መቆየታቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን በወረዳው ሰላም በመስፈኑ ሁሉም በልማት ስራ ላይ ማተኮሩን ጠቅሰው የሰፈነው ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በሰላም ኮንፍረንሱ ላይ የተገኙት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ተመስገን ገቢሳ፣ በወረዳው ህብረተሰቡ ከጸጥታ አካላት ጋር ተቀናጅቶ በመስራቱ አስተማማኝ ሰላም መስፈኑን ገልጸዋል።
የወረዳው ነዋሪዎችም ፊታቸውን በሙሉ አቅም በልማት ስራ ላይ መሰማረራት መቻላቸውን ጠቅሰው የወረዳው አስተዳዳርም የነዋሪውን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ ስራዎችን እየፈጸመ ይገኛል ብለዋል።
የምስራቅ ወለጋ ዞን አስተዳደር እና ፀጥታ ፅህፈት ቤት ሀላፊ ኮለኔል ለሜሳ ኦልጂራ በበኩላቸው ህብረተሰቡ ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ባደረገው አስተዋጽኦ ውጤት መገኘቱን አውስተዋል።
አሁንም በዞኑ የበለጠ ሰላም እንዲሰፍንና የልማት ስራዎች እንዲሳልጡ ህብረተሰቡ ጸረ ሰላም ሀይሎችን ለህግ አካላት አሳልፎ በመስጠት ረገድ አስተዋጽውን ማጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።
በዞኑ እስከ ቀበሌ ድረስ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን የህግ ማስከበር ስራው በተደራጀ መልኩ መቀጠሉን የገለጹት ደግሞ በሀገር መከላከያ ሰራዊት የ101ኛ ኮር የሎጂስቲክ ሀላፊ ኮሎኔል ኢያሱ ሀብቱ ናቸው።
በዞኑ ለተገኘው ሰላም የህብረተሰቡ አስተዋጽኦ ትልቅ እንደሆነ ያስታወሱት ኮለኔሉ የዞኑ ህዝብ የሚያደርገውን ተሳትፎ ማጠናከር እንዳለበት አስገንዝበዋል።