የጂንካ ዩኒቨርሲቲ የእንስሳት ምርታማነትን በማሳደግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት እየሰራ ነው

ጂንካ፤ነሐሴ 15/2017 (ኢዜአ):- የእንስሳት ጤና አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግና የእንስሳት ምርታማነትን በማሳደግ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት እየሰራ መሆኑን የጂንካ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በአሪ እና በደቡብ ኦሞ ዞኖች አርሶና አርብቶ አደር አካባቢዎች የተሻሻለ የእንስሳት ጤና አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።

በደቡብ ኦሞ እና በአሪ ዞን በተካሄደው የፕሮጀክት ማስጀመሪያ ፕሮግራም  የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዚዳንት መልካሙ ዘሮ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ አካባቢው በርካታ የእንስሳት ሀብት ያለበት በመሆኑ የእንስሳቱን ጤና በመጠበቅና ዝርያ በማሻሻል ምርቱን በእጥፍ ለማሳደግ እየተሰራ ይገኛል።

ዛሬ በዩኒቨርሲቲው ይፋ የተደረገው ፕሮጀክትም የእንስሳት ጤና አገልግሎት ተደራሽ ባልሆነባቸው ገጠራማ አካባቢዎች አገልግሎቱን በቅርበት ተደራሽ በማድረግ ማህበረሰቡን ለማገዝ ያስችላል ብለዋል።

የዩኒቨርስቲው የእንስሳት ጤና ሳይንስ የትምህርት ክፍል ተመራማሪ እና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዱባለ በየነ (ዶ/ር) ፕሮጀክቱ ሁለት ዋና አላማዎችን ይዞ የተቋቋመ መሆኑን ጠቅሰው የአርሶና የአርብቶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ ያማከለ የተሻሻለ የእንስሳት ጤና አገልግሎት መስጠት ዋነኛ አላማው እንደሆነም ጠቁመዋል።

እንዲሁም በእንስሳት ህክምና ተመርቀው ስራ ያላገኙ ወጣቶችን በማደራጀትና የህክምና ቡድን በማቋቋም በጤና ባለሙያዎች እጥረት ምክንያት አገልግሎቱ ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች ለመገኘት ፕሮጀክቱ እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ለፕሮጀክቱ ትግበራ ዩኒቨርስቲው ለጤና ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት፣ መድኃኒቶችን እና የህክምና ቁሳቁሶችን በማሟላት እገዛ እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በባካዳውላ አሪ ወረዳ ሴኔጋል ቀበሌ በተካሄደው የፕሮጀክት ማስጀመሪያ መረሃ ግብር ላይ የተገኙት የአሪ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ፥ አካባቢው የተሻሻለ የእንስሳት ዝርያ በስፋት የሚገኝበትና በሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የወተት ክላስተር እንዲሆኑ ከተመረጡ አካባቢዎች አንዱ መሆኑን ገልጸዋል።

የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ዛሬ ይፋ ያደረገው ፕሮጀክትም የእንስሳቱን ጤና በማሻሻል ምርታማነትን ለመጨመር አጋዥ እንደሆነም ተናግረዋል ።

በደቡብ ኦሞ ዞን እና በአሪ ዞን እየተተገበረ ባለው ፕሮጀክት ተጠቃሚ ከሆኑ የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች መካከል ወጣት አብነት ሶይተየር እና  ገነት ገረሙ ይገኙበታል።

ወጣቶቹ ዩኒቨርስቲው ይፋ ባደረገው ፕሮጀክት የስራ ዕድል ማግኘታቸውን ጠቅሰው በሰለጠኑበት የሙያ መስክም በቅርበት ማህበረሰባቸውን ለማገልገል ዕድል በማግኘታቸው መደሰታቸውንም ገልፀዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም