ኢጋድ እና ጃፓን ወጣቶችን በማብቃት፣ ሰላም እና መረጋጋት ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማሙ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2017 (ኢዜአ)፡- የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን(ኢጋድ) እና ጃፓን  ወጣቶችን በማብቃት፣ ሰላም እና መረጋጋት ላይ ያላቸውን ትብብር ለማጠናከር ተስማምተዋል።

በጃፓን ዮካሃማ ከተማ እየተካሄደ የሚገኘው ዘጠነኛው የጃፓን አፍሪካ ልማት ዓለም አቀፍ ፎረም(ቲካድ) ዛሬ ሁለተኛ ቀኑን ይዟል።

የኢጋድ ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር) ከፎረሙ ጎን ለጎን ከተለያዩ ሀገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች ጋር የሁለትዮሽ ውይይቶችን እያካሄዱ ይገኛሉ።

ዋና ፀሐፊው ከጃፓን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ፉጂ ሂሳዩኪ ጋር ምክክር አድርገዋል።

በውይይቱ ሁለቱ ወገኖች በዜጎች ደህንነት ጥበቃ፣ ወጣቶችን ማብቃት፣ ሰላም እና መረጋጋት ላይ ያላቸውን ግንኙነት ለማጠናከር ተስማምተዋል።

ዋና ፀሐፊው ጃፓን በሴቶች ጉዳይ፣ በሰላምና ደህንነት እንዲሁም ለኢጋድ የአመራር አካዳሚ እያደረገች ላለው ጠንካራ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ኢጋድ እና ጃፓን የሁለትዮሽ ትብብራቸውን የሚያጠናክር ስምምነት እ.አ.አ በ2016 መፈራረማቸውን ኢዜአ ከቀጣናዊ ተቋሙ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።

ዘጠነኛው የጃፓን አፍሪካ ልማት ዓለም አቀፍ ፎረም(ቲካድ) ነገ ይጠናቀቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም