ቀጥታ፡

በክልሉ በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በቂ ምርት በማቅረብ ዋጋን ለማረጋጋት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ቢሮው

ሚዛን አማን፤ ነሐሴ 15/2017(ኢዜአ)፡- በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በቂ ምርት በማቅረብ ዋጋን ለማረጋጋት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታውቋል።

በክልሉ ሕገ ወጥ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት ለመከላከልም ግብረ ኃይል መቋቋሙን ቢሮው ገልጿል።

የቢሮው ኃላፊ ተመስገን ከበደ ዛሬ በሰጡት መግለጫ በክልሉ በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች በቂ ምርት በማቅረብ ዋጋን ለማረጋጋት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ምርትና ምርታማነትን በመጨመር የዜጎችን የመግዛት አቅም ማሳደግ ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ለመንግስት ሠራተኛው የደመወዝ ጭማሪ እንደሚደረግ ይፋ መደረጉን ተከትሎ ሕገወጥ የንግድ እንቅስቃሴ እንዳይከሰት የመከላከል ተግባር ቅድሚያ ተሰጥቶት እንደሚከናወንም የቢሮ ሀላፊው አስታውቀዋል።

ለዚህም በክልሉ ሁሉም መዋቅሮች ግብረ ኃይል መቋቋሙን እንዲሁም የምርት እጥረት እንዳያጋጥምና ያልተገባ ዋጋ በሚጨምሩ ነጋዴዎች ላይ ጥብቅ ክትትል ይድረጋል ብልዋል።

ነዳጅ ላይ በልዩነት ቁጥጥር ይድረጋል ያሉት ቢሮ ኃላፊው፣ ለሁለት ዓመት የቤት ኪራይ ጭማሪ እንዳይደረግ ከአምና ጀምሮ እየተሰራበት ያለው አዋጅ መጣስ እንደሌለበትም አሳስበዋል።

በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ለሸማቹ በቂ ምርት በማቅረብ ዋጋን ለማረጋጋት የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

ኅብረተሰቡ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ሲያጋጥመው ለቢሮው ፈጥኖ ጥቆማ በማድረስ መብቱን እንዲያስጠብቅም ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም