አዳዲስ የመስህብ መዳረሻ የልማት ሥራዎች የሀገሪቱ ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅም ሆነዋል - ሚኒስቴሩ - ኢዜአ አማርኛ
አዳዲስ የመስህብ መዳረሻ የልማት ሥራዎች የሀገሪቱ ተጨማሪ የኢኮኖሚ አቅም ሆነዋል - ሚኒስቴሩ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2017(ኢዜአ)፡- በቱሪዝም ዘርፍ የተከናወኑ አዳዲስ የመስህብ መዳረሻ የልማት ሥራዎች ዘርፉን በማነቃቃት የኢኮኖሚ አቅም እየሆኑ መምጣታቸውን የቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።
በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የተጀመረውን ፈጣን እድገት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት ከተሰጣቸው አምስት ቀዳሚ ዘርፎች መካከል ቱሪዝም አንዱ ነው።
የቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ እንደገና አበበ(ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በቱሪዝም ሃብት የታደለች ብትሆንም ከዘርፉ ያላት ተጠቃሚነት እምብዛም ሆኖ ቆይቷል።
የለውጡ መንግስት ለዘርፉ የሰጠውን ልዩ ትኩረት ተከትሎ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚከናወኑ የቱሪዝም ልማቶች በከፍተኛ ሁኔታ ጨምረዋል፡፡
ይህም ዘርፉ እንዲነቃቃ ከማስቻሉ ባለፈ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያለው አስተዋጽኦ እንዲያድግ እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
ለተገኘው ለውጥ የአመራር ቁርጠኝነት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቁመው፤ ለስኬቱ የቱሪዝም ዘርፉን እይታ ማስፋትና ተቋማዊ ሪፎርም ማከናወን አንዱና ዋነኛው መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ሀገሪቱ ያላትን ሃብት መለየት፣ ማልማትና ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ አዳዲስ የመዳረሻ ስፍራዎችን መገንባትም እንዲሁ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን አብራርተዋል።
የግል አልሚዎች ከመንግስት ጋር በመተባበር በቱሪዝም ልማት እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠር የሚቻሉባቸው አሰራሮች ተግባራዊ መደረጋቸውንም አክለዋል።
በተለይም የቱሪዝም ዘርፉ የሚፈጥረውን የስራ እድል በአግባቡ መጠቀም እንዲቻል አካታች የቱሪዝም ልማት ትኩረት እንደተሰጠው ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።
እንዲሁም የሰው ሃይሉን ማብቃት የሚያስችሉና አገልግሎት አሰጣጡን የሚያዘምኑ በቴክኖሎጂ የታገዙ አሰራሮችን በማስረጽ ዘርፉ ራሱን እንዲያጎለብት አስቻይ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን ጠቅሰዋል።
ቱሪዝም የሀገሪቱ የእድገት ግስጋሴ አንዱ ተስፋ መሆኑ ታምኖበት እየተከናወኑ ለሚገኙ ተግባራት ስኬት መሰል ስራዎች ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ከተግባራቱ መካከል ለ16 ዓመታት ጥቅም ላይ የዋለውን ፖሊሲ ማሻሻል አንዱና ዋነኛው ሲሆን፤ ይህም የዘርፉን ተወዳዳሪነትና ውጤታማነት ለማሳደግ እድል እንደሚፈጥር ታምኖበታል።
በአዲስ አበባ የተከናወነው ገበታ ለሸገር ፕሮጀክትን ጨምሮ በገበታ ለሃገርና በገበታ ለትውልድ የለሙ መዳረሻዎች ትልቅ ማሳያ መሆናቸውንም አክለዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ ክልሎች የተገነቡና በመገንባት ላይ የሚገኙ አየር ማረፊያዎች ለቱሪዝም ዘርፉ ማንሰራራት ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ቀደም ሲል ከቪዛ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር የነበረውን የተንዛዛ ሒደት ማስቀረት የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ መደረጉ ለቱሪስት ፍሰት መጨመር ጉልሀ አስተዋጽኦ ማበርከቱንም ነው የገለጹት።
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን እንደጎበኙ ጠቅሰው፤ በዚህም 4 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘት መቻሉን ሚኒስትር ዴኤታው አብራርተዋል።
ይህ ውጤት የለውጡ መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረት የተገኘ መሆኑን ገልጸው፤ ቱሪዝምን የማልማትና ጠቀሜታውን የማጉላት ስራው ይበልጥ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።