የውሃ ስማርት ቴክኖሎጂዎችን ለገጠር ማህበረሰብ በሰፊው ተደራሽ ይደረጋል - ኢንስቲትዩቱ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2017(ኢዜአ)፡- በቀላሉ ጥቅም ላይ የሚውሉ የውሃ ስማርት ቴክኖሎጂዎችን ለገጠሩ ማህበረሰብ በሰፊው ተደራሽ ለማድረግ ዝግጅት መጠናቀቁን የኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡

የኢንስቲትዩቱ ቴክኒካል ድጋፍ መሪ ስራ አስፈጻሚ አይችሉህም ዘነበ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢንስቲትዩቱ የውሃ አቅርቦትን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎች እንዲተላለፉ እያደረገ ይገኛል፡፡

በበጀት ዓመቱ በቀላሉ ጥቅም ላይ የሚውሉ የውሃ ስማርት ቴክኖሎጂዎችን ለገጠሩ ማህበረሰብ በሰፊው ማሰራጨት የሚያስችል ዝግጅት እየተጠናቀቀ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ቴክኖሎጂዎቹን ከከተማ በራቁና የውሃ ተጠቃሚ ባልሆኑ አካባቢዎች በሰፊው ለማሰራጨት 21 ሳይቶች መለየታቸውን ጠቁመው፤ አካባቢዎቹ ከአምስት እስከ አስር ሜትር ባለ ርቀት ከመሬት ውስጥ በቀላሉ ውሃ የሚገኝባቸው መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የቴክኖሎጂዎቹ ውጤታማነት ፍተሻ ተካሂዶባቸው ጥራታቸው መረጋገጡን ስራ አስፈጻሚው ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

ቴክኖሎጂዎቹ ለመጠጥ፣ ለምግብ ማብሰያ፣ ለመታጠቢያ እንዲሁም ለእንስሳትና ለጓሮ አትክልት የሚሆን ውሃ ለመሳብ ያላቸው ጠቀሜታ የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ኢንስቲትዩቱ በውሃ ቴክኖሎጂ ዘርፍ ከሰላሳ አንድ በላይ በሚሆኑ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት ለሚማሩ 2ሺህ 500 በላይ ሰልጣኞች የቴክኒክ ድጋፍ ማድረጉን አንስተዋል።

ኢንስትቲዩቱ በኤሌክትሮኒክ ሜካኒካል፣ በድሪሊንግ፣ በወተር ሰፕላይ፣ በኢሪጌሽን ድሬኒንግ ቴክኖሎጂ ምዘና እየሰጠ መሆኑንም አስታውቀዋል፡

ተቋሙ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ከ2 ሺህ 500 በላይ ለሆኑ የውሃ ባለሙያዎች የብቃት ማረጋገጫ ምዘና መስጠቱን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም