የተተገበሩ የአሠራር ማሻሻያዎች የሲሚንቶ ግብይትን አረጋግተዋል - ኢዜአ አማርኛ
የተተገበሩ የአሠራር ማሻሻያዎች የሲሚንቶ ግብይትን አረጋግተዋል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 15/2017 (ኢዜአ)፡- እየተተገበሩ ያሉ ቁልፍ የአሠራር ማሻሻያዎች የሲሚንቶ ግብይቱን በከፍተኛ ሁኔታ እንዳረጋጉት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።
አሁን ላይ የሲሚንቶ ንግድ በተጨባጭ መረጋጋቱን ያነሱት በሚኒስቴሩ የሀገር ውስጥ ግብይት መሪ ሥራ አስፈጻሚ ሊቁ በነበሩ፤ ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን ጠቅሰዋል።
የመጀመሪያው አዳዲስ ፋብሪካዎች ጭምር ወደ ምርት በመግባታቸው በቂ የምርት አቅርቦት እንዲኖር ማስቻሉ ነው ብለዋል።
እንዲሁም በሲሚንቶ ግብይት ሥርዓት ላይ ማሻሻያዎች መደረጋቸውና ዋጋውም ገበያ መር እንዲሆን መወሰኑ መሆኑን ነው ለኢዜአ የተናገሩት።
በኢስት አፍሪካ ናሽናል ዲስትሪቢዩሽን የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ማናጀር አሸናፊ መለሠ፤ ለሚ እና ድሬዳዋ ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካዎች አሁን ላይ የገበያውን ከ45 በመቶ በላይ ፍላጎት መሸፈናቸውን አንስተዋል።
በተጨማሪም በተቀላጠፈና ከ3ኛ ወገን በፀዳ የዲስትሪቢውሽን ሥርዓትና በዘመናዊ የጭነት ተሽከርካሪዎቹ አማካኝነት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የምርት ሥርጭቱን እያከናወነ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ይህን ተከትሎም የአንድ ኩንታል ሲሚንቶ ዋጋ በአዲስ አባባ በሚገኙ አከፋፋዮች ዘንድ ቀደም ሲል ከነበረበት ዋጋ ከግማሽ በላይ እንዲቀንስ በማድረግ እና በዚህም የተረጋጋ ግብይት መዘርጋቱን ነው ያረጋገጡት።
ለሚ ናሽናል ሲሚንቶ በቀን 150 ሺህ ኩንታል እያመረተ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሐዋሳ፣ አዳማ እና ጅማ ምርቱን በፍጥነት ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ዴፖዎች ከመኖራቸውም በተጨማሪ በመላው ኢትዮጵያ የምርት ስርጭት መኖሩን ጠቁመዋል።
በቂ ምርት ወደ ገበያ ማቅረብ በመቻሉ ግብይቱን ከማረጋጋት በተጨማሪ የግንባታው ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲነቃቃ ማስቻሉንም አመላክተዋል።