ኢትዮጵያ በምታስተናግደው የአየር ንብረት ጉባኤ አዲስ አበባን ይበልጥ ለዓለም ለማስተዋወቅ በቂ ዝግጅት ተደርጓል-ኮሚሽኑ - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በምታስተናግደው የአየር ንብረት ጉባኤ አዲስ አበባን ይበልጥ ለዓለም ለማስተዋወቅ በቂ ዝግጅት ተደርጓል-ኮሚሽኑ
አዲስ አበባ ፤ ነሐሴ 15/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ በምታስተናግደው ሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ አዲስ አበባን ይበልጥ ለዓለም ለማስተዋወቅ በቂ ዝግጅት መደረጉን የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
ኢትዮጵያ በምታስተናግዳቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ሳምንት፣ ሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ እና ሁለተኛው የካሪቢያን እና የአፍሪካ መሪዎች ጉባዔዎች ከ25 ሺህ በላይ ታዳሚዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።
አዲስ አበባም እነዚህን ጉባዔዎች በሚገባው ልክ ለማስተናገድ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማጠናቀቅ እንግዶቿን እየተጠባበቀች ትገኛለች፡፡
ዝግጅቱን አስመልክቶ የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ በመዲናዋ በተከናወኑ በርካታ ዓለም አቀፍ ሁነቶች ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቁ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
የተመዘገበው ውጤት በከተማዋ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ሁነቶች እንግዶችን ከማስተናገድ ባሻገር፣ በከተማዋ የሚኖራቸውን ቆይታ ለማራዘም የሚረዱ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የሚያመላክት እንደሆነም ገልፀዋል።
በ2017 ዓ.ም ብቻ በመዲናዋ ከ150 በላይ አለም አቀፍ እና አህጉር አቀፍ ሁነቶች መካሄዳቸውን አስታውሰዋል፡፡
በቀጣይ በሚካሄዱት ሶስት ጉባኤዎች ለመሳተፍ ለሚመጡ እንግዶች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ለመስጠት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ባለድርሻ አካላት ኢትዮጵያዊነትን የሚያንጸባርቅ መልካም መስተንግዶ ከመስጠት ባለፈ ታዳሚዎቹ ስለአገሪቱ በጎ ምልከታ እንዲኖራቸውና የማይረሳ ትዝታን ይዘው እንዲሄዱ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈ የመዲናዋን የቱሪዝም መዳረሻዎች በማስጎብኘት የጉባዔው ታዳሚዎች ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ የሚያስችል በቂ ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ጠቅሰዋል፡፡
ጉባኤው የተሳካ እንዲሆን ከዘርፉ ባለሞያዎች ባሻገር ነዋሪዎችም የከተማዋ አምባሳደር በመሆን በኢትዮጵያዊነት ባህል እንግዶችን በመቀበልና በማስተናገድ የሁልጊዜ ትብብራቸውን እንዲወጡ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ ሆቴል ባለንብረቶች ማህበር ፕሬዝዳንት ወይዘሮ አስቴር ሰለሞን በበኩላቸው፤ በመዲናዋ የሚካሄዱ አለም አቀፋዊ እና አህጉራዊ ሁነቶች ለዘርፉ ትልቅ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተሰሩ መሰረተ ልማቶች ከተማዋን ከፍ ወዳለ ደረጃ እየወሰዷት መሆኑን ተከትሎ የሆቴል ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ሁኔታ እየተነቃቃ እንደሚገኝም አብራርተዋል፡፡
በጉባኤው ለመሳተፍ ለሚመጡት እንግዶች ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ሆቴሎች በቂ ዝግጅት ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያን ባህል በሚሳይና ፍጹም ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ መስተንግዶ ለመስጠት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል፡፡