የወንዝ ዳርቻ ልማት ለመላው አፍሪካ ምልክትና አርአያ የሚሆን ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የወንዝ ዳርቻ ልማት ለመላው አፍሪካ ምልክትና አርአያ የሚሆን ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2017(ኢዜአ)፦ የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ለመላው አፍሪካ ልክ እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ምልክትና አርአያ መሆን እንደሚችል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) "የመደመር መንግስት" የተሰኘውን መጽሐፋቸውን በተመለከተ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም በመደመር ሐሳብ ላይ ያተኮሩ መደመር፣ የመደመር መንገድ እና የመደመር ትውልድ የተሰኙ ሦስት መጽሐፍትን ለንባብ ማብቃታቸው ይታወቃል፡፡
"የመደመር መንግስት" የተሰኘው 4ኛ መጽሐፍ በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት፤ በአሁኑ ወቅት የኮሪደር ልማት ስራዎች ምስክርነት እየተሰጠባቸው ነው ብለዋል።
ለማሳያነትም እንጦጦ ሽሮሜዳ አካባቢ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ከ700 በላይ አዳዲስ የቢዝነስ ሱቆች መከፈታቸውን ጠቁመው፤ ይህም ለበርካታ ሰዎች የስራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
የወንዝ ዳርቻ ልማት ለበርካታ ሰዎች የቢዝነስና የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ጠቁመው፤ ለመላው አፍሪካ ልክ እንደ አረንጓዴ ዐሻራ ምልክትና አርአያ ሊሆን የሚችል ስራ ነው ብለዋል።
የኮሪደር ልማት በተለያየ መልኩ ስራ መፍጠር፣ የሀገርን ገጽታና ምልከታ መቀየር እንዲሁም ጤናማነትን ማረጋገጥ የቻለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ለሁሉም አፍሪካ ምሳሌ መሆን የሚችል እንደሆነ አንስተው፤ በአሁኑ ወቅት የአፍሪካ መሪዎች ልዑካን እየላኩ ልምድ የሚቀስሙበትና የሚቀምሩበት ነው ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ የከተማ ኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማትና የገጠር ኮሪደርና ፕሮጀክቶች የሚጨበጡ፣ የሚታዩ ስራዎች መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
ስራዎቹ ኢትዮጵያውያን በሙሉ ሊኮሩባቸው የሚገቡ ልማቶች መሆናቸውን አንስተው፤ እጅግ የሚያኮራ በመደመር መንግስትና በህዝብ መካከል ባሉ የጋራ ራዕይ ስነቃ የተገነቡ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
የኮሪደር ልማት ከፍተኛ ምሳሌያዊ ስራ ሆኖ ለብዙ ሀገራት የሚያገለግል፤ የመደመር ትውልድ በዘመኑ ውስጥ ያስቀመጠው አሻራ፣ የማይናወጥና አኩሪ ተግባር መሆኑንም አብራርተዋል፡፡