የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለናይል ተፋሰስ ሀገራት ትብብር አዲስ ምዕራፍን የሚከፍት ነው- ከፍተኛ የውሃ ሀብቶች ባለሙያ ኢንጂነር ጌቱ ቢፍቱ - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለናይል ተፋሰስ ሀገራት ትብብር አዲስ ምዕራፍን የሚከፍት ነው- ከፍተኛ የውሃ ሀብቶች ባለሙያ ኢንጂነር ጌቱ ቢፍቱ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2017(ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ ለናይል ተፋሰስ ሀገራት አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑን በካናዳ አልበርታ ግዛት ተቀማጭነታቸውን ያደረጉት የውሃ ሀብቶች ከፍተኛ ተመራማሪ (Senior Hydrologist) ኢንጂነር ጌቱ ቢፍቱ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ በብዙ ልፋትና መስዋእትነት የተገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በመስከረም ወር እንደሚመረቅ ተናግረው ነበር።
በመሆኑም የተፋሰሱ ሀገራት በዚህ ታላቅ ቀን እንዲገኙና የጋራ ተጠቃሚነትን በተግባር እንዲመለከቱም ጥሪ አቅርበዋል።
በካናዳ አልበርታ ግዛት ተቀማጭነታቸውን ያደረጉት የውሃ ሀብቶች ከፍተኛ ተመራማሪ(Senior Hydrologist) ኢንጂነር ጌቱ ቢፍቱ የአፍሪካ ግዙፉ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የሆነው ህዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያ ትልቅ የታሪክ ስኬት ከመሆኑ ባሻገር ለናይል ተፋስስ ሀገራት አዲስ የትብብር ምዕራፍ የሚከፍት መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል።
ግድቡ ለከባቢ አየር፣ ለኢኮኖሚ እና ለማህበራዊ ጉዳዮች ካለው ትሩፋት ባለፈ የቀጣናዊ ትብብርና አይበገሬነት ተምሳሌት ነው ብለዋል።
ህዳሴ ግድብ በሀይል ንግድ፣ በጋራ ልማት እና በፖለቲካዊ ትብብር አማካኝነት የአፍሪካ ቀንድ እና ምስራቅ አፍሪካን የማስተሳሰሪያ ገመድ እንደሆነ ተናግረዋል።
ከፍተኛ ባለሙያው ለተፋሰሱ ሀገራት ህልውና የሆነውን የናይል ወንዝ ዘላቂ እና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ለመጠቀም በትብብር መስራት እንደሚያስፈልግም መክረዋል።
በመተማመን እና በመተባበር የውሃ ሀብቱን ለጋራ ብልጽግና መሰረት ወደ ማድረግ ማሸጋገር እንደሚቻልም ነው ከፍተኛ ተመራማሪው የገለጹት።
ግድቡን የብሄራዊ የልማት ግቦችን ከቀጣናዊ ፍላጎቶች፣ ድንበር ተሻጋሪ አጋርነቶች እና ከተቋማዊ ግንኙነት ጋር የበለጠ በማስተሳሰር የቀጣናው የሰላም እና መረጋጋት አቅም እንዲሆን ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።
ግድቡ በአፍሪካ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ባረጋገጠ መልኩ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ስኬታማ በሆነ መልኩ መገንባት እንደሚቻል በተግባር ያሳየ መሆኑን አመልክተዋል።
ባለሙያው የናይል ተፋሰስ ሀገራት በቁርጠኝነት፣ በትብብር መንፈስ እና በጋራ ራዕይ ቀጣናውን የዘላቂ ልማት እና መረጋጋት ተምሳሌት ለማድረግ እንዲሰሩም ጥሪ አቅርበዋል።