የአፍሪካ  ሀገራት ኢ-ተገማች በሆነችው ዓለም አይበገሬነት መገንባት እና የኢኖሼሽን መፍትሄዎችን መተግበር ይኖርባቸዋል - ህብረቱ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2017(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ሀገራት ለተለዋዋጭ እና ኢ-ተገማች ዓለም የሚሆን ጠንካራ አቅም መገንባት እና የኢኖሼሽን መፍትሄዎችን መተግበር እንደሚገባቸው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ ገለጹ። 
 
ዘጠነኛው የጃፓን አፍሪካ ልማት ዓለም አቀፍ ፎረም (ቲካድ) ዛሬ በዮካሃማ መካሄድ ጀምሯል።

በፎረሙ ላይ የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር ሺገሩ ኢሺባ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ፣ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የአንጎላ ፕሬዝዳንት ጆአኦ ሎሬንቾና የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል።

“የአፍሪካ እና ጃፓን የጋራ መፍትሄዎችን መፍጠር”  የፎረሙ መሪ ሀሳብ ነው። 

የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር መሐሙድ አሊ ዩሱፍ በፎረሙ ላይ ባደረጉት ንግግር አፍሪካና ጃፓን ለሶስት አስርት ዓመታት የዘለቀ ወዳጅነት እንዳላቸው ገልጸዋል። 

ሁለቱ ወገኖች ዘላቂና መዋቅራዊ የልማት ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል የፈጠራ መፍትሄዎችን በጋራ መቅረጽ እንደሚገባቸው አመልክተዋል።

ኢኖቬሽን የሀገራቱ ትብብር የማጠናከር አካል ማድረግ እንደሚያስፈልግ የገለጹት ሊቀ መንበሩ ዘርፉ አካታችነትን ለማረጋገጥ ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ተናግረዋል።

ሊቀ መንበሩ አህጉራዊ ማዕቀፎችን አንስቶ ባነሱት ሀሳብ ላይ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና (AfCFTA) ለንግድ፣ ኢንዱስትሪ እና ለፈጠራ ስራ እድገት አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑን ነው የገለጹት።

አጀንዳ 2063 ከቲካድ እና ከዘላቂ ልማት ግቦች ጋር የተቆራኘ መሆኑን ተናግረዋል። 


 

ፎረሙን በጋራ ያዘጋጀው የዓለም ባንክ የአፍሪካ የረጀም ጊዜ ራዕይ ለማሳካት የሚያስችል የፋይናንስ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል። 

ከጂኦ ፖለቲካ አኳያም በዓለም ላይ ያለው አለመራረጋጋት በአፍሪካ የልማት አጅንዳዎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖዎች እያሳደረ ነው ብለዋል ሊቀ መንበሩ።

የፋይናንስ አቅርቦት መቀነስ፣ የታሪፍ ጫናዎች ፣ ኢ-ተጋማችነት እና ተለዋዋጭ ሁኔታዎች የአፍሪካን ለውጥ እያስተጓጎሉ መሆኑን ገልጸዋል።

የአፍሪካ ሀገራት ያሉ ፈተናዎችን የሚቋቋም አቅም መፍጠር እና የኢኖሼሽን መፍትሄዎችን መተግበር እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።   

አፍሪካ እና ጃፓን ዘላቂ፣ ለውጥ አምጪና ሁሉን አካታች እድገት የሚያመጡ የኢኖሼሽን ውጤቶች ለመጠቀም በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

የአፍሪካ መጻኢ ጊዜ በአይበገሬነት፣ በፈጠራ እና ኢኖቬሽንን መሰረት ያደረገ ዓለም አቀፍ አጋርነት የሚወሰን መሆኑን ሊቀ መንበሩ አስገንዝበዋል።

ዘጠነኛው የጃፓን አፍሪካ ልማት ዓለም አቀፍ ፎረም (ቲካድ) አስከ ነሐሴ 16 ቀን 2017 ዓ.ም ይቆያል።

እ.አ.አ በ1993 የተጀመረው የጃፓን አፍሪካ ልማት ዓለም አቀፍ ፎረም (ቲካድ) አፍሪካ እና ጃፓን በልማት፣ ሰላም እና ደህንነት ያላችውን ትብብር በባለብዙ ወገን ትብብርና አጋርነት ማጠናከር አላማ ያደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም