ቀጥታ፡

ከወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ እያደገና ውጤት እያመጣ ያለው ግልጽ በሆነ ራዕይና ግብ እየተመራ በመሆኑ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2017(ኢዜአ)፦ ከወጪ ንግድ የሚገኘው ገቢ እያደገና ውጤት እያመጣ ያለው ግልጽ በሆነ ራዕይና ግብ እየተመራ በመሆኑ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚነኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

በ2018 በጀት ዓመት ሐምሌ ወር ብቻ ከወጪ ንግድ 830 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማሳያነት አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የመደመር መንግሥት የተሰኘውን አዲስ መጽሐፋቸውን በተመለከተ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቃለ መጠይቅ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ሰባት ዓመታት በርካታ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙም እጅግ አስደናቂ እና ለትውልድ የሚሻገሩ አስደማሚ ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።

መንግስት ቆመው የነበሩ ፕሮጀክቶችን ከማስቀጠል አኳያ ስኬታማ ስራ ማከናወኑን ገልጸው የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

በግብርናው ዘርፍም እንዲሁ አኩሪ ተግባራት መከናወናቸውንና ጋዝን ጨምሮ የማዕድን ሀብቶችን አውጥቶ የመጠቀም ህልም መሳካቱንም ገልጸዋል።

በኮሪደር ልማት አማካኝነት ከተሞች መዘመናቸውንና በልማት ስራ የሚታዩ ለውጦች መመዝገባቸውንም ነው ያነሱት።

ኢኮኖሚው በማንሰራራት ላይ ይገኛል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኤክስፖርት ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ መመዝገቡን ገልጸዋል።

በአዲሱ 2018 በጀት ዓመት ሐምሌ ወር ብቻ ከኤክስፖርት 750 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 830 ሚሊዮን ዶላር መገኘቱን ጠቁመዋል።

ይህም በ2017 በጀት ዓመት ሐምሌ ወር ተገኝቶ ከነበረው 350 ሚሊዮን ዶላር የወጪ ንግድ ገቢ አንጻር ሲታይ ከፍተኛ ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል።

የኤክስፖርት ዘርፉ እያደገና ውጤት እያመጣ ያለው ግልጽ በሆነ ራዕይና ግብ እየተመራ በመሆኑ ነው ሲሉም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም