ቀጥታ፡

የመደመር መንግስት ከተማን ከማዘመን ጎን ለጎን የተሻገረ ገጠርን ለመፍጠርም እየሰራ ነው - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2017(ኢዜአ)፦የመደመር መንግስት ከተማን ከማዘመን ጎን ለጎን የተሻገረ ገጠርን ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ቀደም በመደመር ሐሳብ ላይ ያተኮሩ መደመር፣ የመደመር መንገድ እና የመደመር ትውልድ የተሰኙ ሦስት መጽሐፍትን ለንባብ ማብቃታቸው ይታወቃል፡፡

በዚሁ ሐሳብ ላይ የጻፉትን "የመደመር መንግስት" የተሰኘውን አራተኛ መጽሐፍ በተመለከተ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ አድርገዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እንደገለጹት፤ የመደመር መንግስት ከተማና ከተሜነትን በዝርዝር በመገንዘብ የተገበረው የኮሪደር ልማት ያመጣውን ውጤት ማየት አስቸጋሪ አይሆንም፡፡

ከተሜነት የሰው ልጅ የብልጽግና መደራሻ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከተሜነት የሰው ልጆች ኑሮን ምቹ የሚያደርግ፣ አገልግሎትን የሚያቀል፣ ነገሮች በተሻለ መንገድ የሚያሟሉበት የኑሮ ዘዬን መፍጠር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

የሕክምና አገልግሎት፣ ትምህርትና ትራንስፖርት፣ በቀላሉ ማግኘት የሚያስችል መሆኑን ጠቁመው፤ ሰዎች ህይወታቸውን በቀላሉ መምራት የሚያስችላቸው እና መዘመንን የሚያመጣ የኑሮ ዘዬ ከተሜነት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከተማ እና ከተሜነትን በአራት ጉዳዮች መመልከት እንደሚቻል ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከማህበራዊ ዕይታ አኳያ ከተሞች የቅይጥ ባህል መፈጠሪያ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከተሜነት ደግሞ ስርዓት ያለው ህብራዊ አንድነትን እንደሚፈጥር ጠቁመው፤ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ እምነቶች ያላቸው ሰዎች ስርዓት ባለው ፍሰት ውስጥ በጋራ እንደሚኖሩት አብራርተዋል፡፡ 

ከኢኮኖሚ አኳያም ከተሞች ለንግድ፣ ለኢንዱስትሪ፣ ለስራ ፈጠራ፣ ለቴክሎጂ ቅርብ መሆናቸውን ጠቁመው፤ ይህም ከተሞች ብዙ ንግድ፣ ኢንዱስትሪ፣ ብዙ ፈጠራ ያለበት መሆኑን አንስተዋል፡፡

ከተሜነት ከኢኮኖሚ አንጻር የላቀ የዕድገትና የፈጠራ አንቀሳቃሽ ሞተር መሆኑን ገልጸው፤ ዕድገትና ለውጥን ለማስቀጠልም ከተሞች ላይ ፈጠራን፣ ኢንዱስትሪን ማስፋት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ 

ከፖለቲካ ዕይታ አኳያ ከተሞች የዳበረ የፖለቲካ ስርዓት መፍለቂያ ማዕከላት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ከተሜነት የሲቪክ ባህል መሰረት፣ የስልጣኔ መሠረት፣ በውይይትና ንግግር መፍትሄ ማምጫ ስፍራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

ከአከባቢ ዕይታ አኳያም ከተሞች የሰው ልጅ ከተፈጥሮ ስርዓት ጋር ውስብስብ ስነ-ምህዳር ውስጥ የሚኖርበት ሁኔታ መኖሩን ገልጸዋል፡፡

ከተሜነት የውበት፣ የጤናማነት፣ የዘመናዊነት፣ የአኗኗር ዘዬ መገለጫ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ብልጽግና ለከተማ ዕድገት ከመስራት ጎን ለጎን የተሻገር ገጠር ለመፍጠርም በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ለአብነትም በቅርቡ የሚመረቀው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ የተጀመረው የገጠር ኮሪደር አስደማሚ መሆኑን ጠቁመው፤ በገጠርም በከተማም ብዝሃ ዘርፍ የሆነ ዕይታ መኖሩን አብራርተዋል።

#Ethiopia #Ethiopian_News_Agecy #ኢዜአ

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም