የመደመር መንግሥት መጽሐፍ የወል እንዲሆን በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
የመደመር መንግሥት መጽሐፍ የወል እንዲሆን በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2017(ኢዜአ)፡-የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ሐሳብ የወልና ገዥ እንዲሆን የሚያስቸሉትን በርካታ ሂደቶችን ያለፈ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጽሐፉ ጋር በተያያዘ ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ሐሳብ ጽንሰት ቀደም ያለ መሆኑን አውስተዋል።
የመደመር መንግስት ጽንሰ ሐሳብ በተለያየ ደረጃ ሊተገበር እንደሚችል ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ በግል ልምምዴ መደመር ረዘም ላለ ጊዜ ከእኔ ጋር የነበረ የተለማመድኩት፣ በሠራሁባቸው መሥሪያ ቤቶች የተጠቀምኩበትና ፍሬ ያፈራሁበት ሐሳብ ነው ብለዋል።
ነገር ግን ወደ መንግሥት ሐሳብ ያደገው በሂደት ነው፤ የመንግሥት አቋም ሐሳብ ለመሆንም በርከት ያለ ጊዜ ወስዶበታል ሲሉ ገልጸዋል።
ወደ መንግሥት ሐሳብነት ከመሸጋገሩ በፊትም በስልጠናዎች፣ በሐሳብ መለዋወጦች፣ ሠነዶች በማገላበጥ፣ ተጨማሪ ንባቦችና ምልከታዎች መደረጋቸውን አንስተዋል።
በእነዚህ ሂደቶች ውስጥም ቀመሩ እያደገ፣ እየዳበረና እየሰፋ ከመጣ በኋላ መጽሐፍ መሆን ሲጀምርና ከጀመረ በኋላም ሐሳቡን የወል ለማድረግ በርካታ ሥራዎች ተሠርተዋል ነው ያሉት።
ለአብነትም ስልጠናዎች ተሰጥተዋል፣ ውይይቶች ተካሂደዋል፣ መጽሐፉ ላይ ትችቶች ተደርገዋል፤ በዚህ ሂደትም መጽሐፉ እየዳበረ እየበሰለ፣ ሙሉ ሐሳብ መያዝ እና ሊያሠራ የሚችል ንድፍ መሆን ችሏል ብለዋል።
መጽሐፉ በውስጡ ወደ ኋላ መለስ ብሎ ለራሱ ህልም ትንታኔ የሚፈይዱትን ታሪኮች በመጠኑ እንደሚዳስስና ወደፊት በመራመድም የዓለምን ነገ ብሎም የእኛን በነገ ውስጥ ያለንን ጉዞ ይተነትናል ነው ያሉት።
በተጨማሪም መጽሐፉን የተለየ ያደረገው ከተጨባጭ ልምድ የተቀዳ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቆይታቸው ያብራሩት።
#Ethiopia #Ethiopian_News_Agecy #ኢዜአ