ጥምረቱ አቅምን በማሰባሰብ እና አንድነትን በመፍጠር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ይበልጥ ማጎልበት ዋነኛ ዓላማው ነው - ኢዜአ አማርኛ
ጥምረቱ አቅምን በማሰባሰብ እና አንድነትን በመፍጠር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ይበልጥ ማጎልበት ዋነኛ ዓላማው ነው

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2017(ኢዜአ)፦ የፖለቲካ ጥምረቱ አቅምን በማሰባሰብ እና አንድነትን በመፍጠር የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታን ማጎልበት ዋነኛ ዓላማው መሆኑን የአስራ አንድ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዳሮት ጉምአ ገለጹ፡፡
አስራ አንድ ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት መመስረታቸውን የገለጹ ሲሆን ጥምረት የመሠረቱ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በዛሬው ዕለት የምስረታ ጉባኤያቸውን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ።
የጥምረቱ አስተባባሪ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዳሮት ጉምአ ፤ ጥምረቱ አንድነት ኃይል መሆኑን በሚያምኑ አካላት የተገነባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የጥምረቱ አባል ፓርቲዎች ለሀገር ሰላም፣ ዕድገትና ክብር በጋራ የሚቆሙ እና ኃላቀር የፖለቲካ ባህልን ለመቀየር እንደሚሰሩም ተናግረዋል፡፡
ፓርቲዎቹ የየራሳቸውን ዓላማ በመያዝ ለጋራ ስኬት ጥምረት መፍጠራቸውን ጠቁመው፤ የተሻለ የፖለቲካ ባህልን ለመገንባት ትልቅ ሚና የሚጫወት መሆኑንም ተናግረዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መጣመር የተሻለች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማስተላለፍ እንደሚጠቅም ጠቁመው፤ ለፖለቲካ ባህል መዘመንም የበኩሉን እንደሚወጣም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ሃይሉ በዚሁ ወቅት፤ አቅምን በማሰባሰብ ለጋራ እና ለተሻለ ዓላማ መሥራት መልካም መሆኑን ተናግረዋል።
ልዩነቶችን በማክበር በጋራ መንቀሳቀስ ለጤናማ የፖለቲካ ስርዓት መዳበር ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው መሆኑንም ገልጸዋል።
ጥምረቱ መጪው ሀገራዊ ምርጫ ፍጹም ተዓማኒ እንዲሆን የበኩሉን እንዲወጣ ጠይቀው፤ ቦርዱ ጥምረቱን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ በበኩላቸው፤ የፓርቲዎቹ ጥምረት ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ መጎልበት ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን ገልጸዋል።
ለመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታም ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን ጠቁመው፤ ጥምረቱ ዘላቂ ሰላምን ለመፍጠር እና ለሀገራዊ መግባባት ስኬታማነት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ተናግረዋል።
የዎቻ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ብርሃኑ ዘለቀ በሰጡት አስተያየት ጥምረቱ ለተሻለ የፖለቲካ ስርዓት ግንባታ ትልቅ ፋይዳ ያለው ነው ብለዋል፡፡
ተበታትኖ የሚገኘውን የሰው ኃይል፣ ቁሳቁስ፣ እውቀትና ቴክኖሎጂ በማሰባሰብ ለሀገር ዕድገት የበኩላቸውን ለመወጣት እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡
የከፋ አረንጓዴ ፓርቲ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ወንድሙ ወዱዌሮ በበኩላቸው ጥምረቱ ለመድበለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታና ለሀገር ዕድገት ትልቅ ጥቅም ያለው መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ጥምር ፓርቲ የመሰረቱት አገው ለፍትሕና ዴሞክራሲ፣አገው ብሔራዊ ሸንጎ፣ ትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ የዶንጋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ ሞቻ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣ አርጎባ ብሔረሰብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ፣ አፋር ነፃ አውጭ ግንባር ፓርቲ፣ ከጋሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ፣የካፋ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ድርጅት፣ ካፋ አረንጓዴ ፓርቲ እና የጋምቤላ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ናቸው፡፡