ልምድን ያዘመነው የሌማት ትሩፋት ለአርሶ አደሩ ምግብም ገንዘብም ሆኗል - ኢዜአ አማርኛ
ልምድን ያዘመነው የሌማት ትሩፋት ለአርሶ አደሩ ምግብም ገንዘብም ሆኗል

(በመንበረ ገበየሁ - ከኢዜአ ሀዋሳ ቅርንጫፍ)
የሌማት ትሩፋት በ2015 ዓ.ም ጥቅምት ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) በአርባ ምንጭ ከተማ ይፋ ያደረጉት መርሀግብር ነው፡፡ በምግብ ራስን በመቻል የዜጎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥም ያለመ ነው። መርሀግብሩ በዋናነት የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ተኩረት አድርጓል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ እንደገለጹት መርሃ ግብሩ አርሶና አርብቶ አደሩን የሚያገናኝ ድልድይ በመሆን በልቶ ከማደር በላይ ከምግብ እጥረት ጋር የተያያዘ ታሪካችንን የሚቀይር ነው፡፡ ለመርሀግብሩ ስኬታማነትም መንግስት ዝርዝር ጥናት አድርጎና እቅድ አውጥቶ ወደ ስራ ከገባ ሦስት ዓመታትን እያስቆጠረ ነው፡፡
የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) እንደሚሉት መርሃ ግብሩ የምግብ ሥርአትን በማሻሻል፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ እያገዘ ነው።
ከዚህ በተጨማሪ የእንስሳት ሃብት ልማቱን ውጤት በአምስት እጥፍ እንዳሳደገው ነው የገለጹት።
ዘርፉን በተያዘው በጀት ዓመት ለማሳደግ ከ160 ሚሊዮን በላይ የአንድ ቀን ጫጩቶችን የማሰራጨትና 5 ሚሊዮን የእንሰሳት ዝርያ የማሻሻል ሥራዎች ይሰራሉ። ከዚህ ጎን ለጎን 17 ቢሊዮን ሊትር ወተት፣ 12 ቢሊዮን እንቁላል ለማምረትና የዓሣ እና የማር ምርትንም ለማስፋት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ይናገራሉ።
መርሀግብሩ የክልሎችን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ አድርጎ የተቀረጸ በመሆኑ በሲዳማ ክልልም መርሀግብሩን ውጤታማ ለማድረግ ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡
በክልሉ በሰባት ፓኬጆች በተጀመረው ሥራ የእንስሳት ሃብት ምርታማነትን አሳድጓል። የዓሣ ልማትን ከሀዋሳ ሐይቅ በተጨማሪ በተለያዩ የአሣ መንደሮችና ኩሬዎች መተግበራቸው በሃገር ደረጃ ምሳሌ ሆነዋል ብለዋል ፍቅሩ (ዶ/ር)፡፡
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ የሌማት ትሩፋት ኢኒሺየቲቭን ተከትሎ የእንስሳት ሀብት ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ እያደገ መጥቷል። በዚህም የመኖ እጥረት እየተስተዋለ ቢመጣም መንግስት ችግሩን ለመፍታት አማራጭ የመኖ ልማት ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በዚህም በተያዘው በጀት ዓመት ከ1 ሚሊዮን 750 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተሻሻለ መኖ በማልማት ከ263 ሺህ 500 ኩንታል በላይ የመኖ ዘር ለማሰራጨት መቻሉን ገልጸዋል።
በአርብቶ አደሩ አካባቢ የሚገኙ ሰፋፊ የግጦሽ መሬቶችን ከማልማት በተጨማሪ የተመጣጠነ መኖ ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን የማስፋት ሥራም እየተከናወነ ነው፡፡ የመኖ ልማት ሥራው የእንስሳት ሃብት ልማቱን ምርታማነት ከመጨመር ባሻገር ከምርቱ ጋር ያልተጣጣመውን የእንስሳት ተዋጽኦ ዋጋ መናር የሚያረጋጋና ለአካባቢ ጥበቃ ስራም ጉልህ አበርክቶ ይኖረዋል።
''ዶሮ ቤት ከሌላት ጅግራ ነች'' በሚል መርህ ሞዴል የዶሮ ቤቶችን ግንባታ በማከናወንም ክልሉ በሀገር ደረጃ ቀዳሚ ሲሆን ስራው በዶሮ እርባታው ዘርፍ ለተገኘው ውጤት ጉልህ አበርክቶ አለው፡፡
ልክ እንደቤተሰብ አባል በሰላምታ ልውውጥ ወቅት የእንስሳቱን ጤናንም ለሚጠይቀው የሲዳማ ህዝብ እንስሳት ምግቡም፣ ልብሱም፣ መጦሪያና ገንዘቡም ጭምር ነው፡፡ የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ደግሞይህን የህብረተሰቡን ከእንስሳት ጋር ያለውን ቁርኝት ያጠናከረ፣ ከዘርፉ የሚያገኘውን ጥቅም ለማሳደግ እድል የፈጠረ ነው፡፡
የክልሉ እንስሳትና ዓሣ ሃብት ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ተክሌ ጆምባ እንደሚናገሩት ደግሞ እንስሳት ለክልሉ ህዝብ " በህይወት ያለ ባንክ" ነው፡፡ በዚህም የዶሮ፣ የወተት፣ ዓሣ፣ ንብና ሃር ትልን ጨምሮ በሰባት ፓኬጆች ከ2 ሺህ 600 በላይ መንደሮችን በማደራጀት እያንዳንዱ አርሶ አደር እንዲሳተፍ በመደረጉ መርሃ ግብሩ ብዙዎችን ተጠቃሚ እያደረገና ህይወታቸውን እየቀየረ ነው፡፡
እንደ አቶ ተክሌ ገለጻ በሲዳማ ክልል በ2017 በጀት ዓመት ብቻ በመርሃ ግብሩ ከ500 ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ መርሀግብሩ ከተጀመረ ጀምሮ በእንሰሳት ሃብት ልማቱ ምርታማነት ላይ የተመዘገቡ ውጤቶችም አመርቂ ናቸው፡፡ መርሀግብሩ ሲጀመር ተሰራጭቶ የነበረውን 857 ሺህ የአንድ ቀን ጫጩት ዘንድሮ ወደ 20 ሚሊዮን ማሳደግ ተችሏል።
የእንስሳት ዝርያን ማሻሻል በመቻሉም ለይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና ለአዲስ አበባ ገበያ በየሦስት ቀን እስከ 4ሺህ 500 ሊትር ወተት የማቅረብ አቅም መፈጠሩን አቶ ተክሌ ይገልጻሉ፡፡ በተያዘው በጀት ዓመትም ከ260 ሺህ በላይ ከብቶችን ዝርያ የማሻሻል፣ 158 ሺህ ዘመናዊ የንብ ቀፎዎችን ለማሰራጨት ታቅዶ ወደስራ ተገብቷል፡፡
በክልሉ በዶሮ ልማትና በሌሎችም ፓኬጆች የተጀመሩ ሥራዎችን ምርታማነት የማሳደግ ሥራም ትኩረት ተሰጥቶታል። በዚህም የሌማት ትሩፋት መርሀግብር የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ አቅም እያሳደገ፣ የምግብ ሉአላዊነቱን እያረጋገጠና የሥራ ዕድልም እየፈጠረ መጥቷል ማለት ይቻላል።
በሸበዲኖ ወረዳ የጣራ ሜሳ ቀበሌ ነዋሪው አርሶ አደር ካሳ ካያሞ የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ተግባራዊ መደረጉን ተከትሎ በወተት ላሞችና ዶሮ እርባታ፣ በዓሣና ንብ ማነብ ትኩረት አድርገው እየሰሩ ነው፡፡ የእንስሳት ልማት እንደ ልጅ እንክብካቤን የሚፈልግ በመሆኑ የመኖ ልማት ሥራው ላይ እየተሳተፉ መሆኑንም ገልጸዋል።
የእንስሳት ተረፈ ምርትን ለማዳበሪያነት መጠቀማቸው ለመስኖ ልማት ምርታማነት እያገዛቸው ነው፡፡ የሌማት ትሩፋትም የእሳቸውን ጨምሮ የአካባቢውን አርሶ አደሩ ኢኮኖሚ ከመደገፍ ባለፈ የአናኗር ዘይቤያቸውን እየቀየረው ነው፡፡
የበንሳ ወረዳዋ ሞዴል አርሶ አደር እቴነሽ ታዬ ከንብ ማነብ በተጨማሪ ዓሣና ዶሮ በማርባት የሌማት ትሩፋት መርሀግብር ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ በእንስሳት እርባታ የበነራቸውን ልምድ በሌማት ትሩፋት በማዘመን ይበልጥ ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡ የዓሣ ሃብት ልማትን ኩሬ አዘጋጅተው እያከናወኑ ይገኛሉ። በዘመናዊ ቀፎ የታገዘው የንብ እርበታ ሥራቸውም ከፍተኛ ገቢ እያስገኘላቸው ነው፡፡ ከላሞቻቸውና ከዶሮዎቻቸው የሚያገኙት ወተትና እንቁላል የአመጋገብ ሥርአታቸውን ቀይሮታል። ከዚያም ባለፈ በዓመት እስከ 40ሺህ ብር በማግኘት ኢኮኖሚያቸውን እየደጎሙ ነው።
በሌማት ትሩፋት መርሀግብር ጋር የተደገፈው የእንስሳት ሃብት ልማት ሥራችን ከባህላችን ጋር የተሳሰረ በጠባብ መሬት ብዙ የምናተርፍበት ዘርፍ ነው ሲሉም አርሶ አደር እቴነሽ ገልጸዋል፡፡
በሲዳማ ክልል ደረጃ በህዳር ወር 2015 ዓ.ም በይፋ የተጀመረው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የህይወት ባንካቸው ለሆነው የእንስሳት ሃብት ልማት የፈጠረውን ምቹ እድል ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡