የኢትዮጵያን የፀሐይ ኃይል ልማት ለመደገፍ በቁርጠኝነት እንሰራለን - የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2017(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ያለውን ከፍተኛ የፀሐይ ኃይል ልማት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት (አይ.ኤስ.ኤ.) አስታወቀ።

የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት ዋና ዳይሬክተር አሺሽ ከሀና ለኢዜአ እንደገለጹት÷ ኢትዮጵያ በፀሐይ ኃይል አማራጭ ከፍተኛ የመልማት ጸጋ ያላት ሀገር ናት።

ለዚህ ይረዳ ዘንድ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት የኢትዮጵያን የፀሐይ ኃይል ልማት ለማገዝ በሚያስችል የፕሮጀክትና የፖሊሲ ትብብር ላይ በጋራ ለመስራት የማዕቀፍ ስምምነት መደረጉን ገልጸዋል።


 

በዚህም በኢትዮጵያ 400 ሜጋ ዋት የፀሐይ ኃይል ማመንጨት የሚያስችል ፕሮጀክት ለመገንባት የተጀመረውን ጥረት ለማገዝ ቁርጠኛ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የፀሐይ ኃይል መሰረተ ልማት መስፋፋት የግል ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው አብራርተዋል።

በውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ቅጥር ግቢም 100 ሜጋ ዋት የሚያመነጭ የመኪና ማቆሚያ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ጣሪያ ፕሮጀክት በመገንባት ለአገልግሎት መብቃቱን ገልጸዋል።

በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ለአገልግሎት የበቃው የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በቀጣይ ለሚተገበረው በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የውሃ መሳቢያ ፕሮጀክት ትልቅ መሰረት እንደሚሆን አስገንዝበዋል።

በተጨማሪም የዓለም አቀፍ የፀሐይ ኃይል ጥምረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፀሐይ ኃይል ቴክኖሎጂ የልህቀት ማዕከል ኢትዮጵያዊያን ሙያተኞችን እያሰለጠነ እንደሚገኝ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ የወሰደችው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በግሉ ዘርፍ የሚመራ ዕድገትና ኢንቨስትመንትን ማፋጠን የሚያስችል መሆኑንም አብራርተዋል።

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው በፀሐይ ኃይል ልማት ዘርፍ የግሉን ዘርፍ የኢንቨስትመንት ፍሰት ለማሳደግ ጉልህ ጠቀሜታ እንዳለው ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት የማይበገር የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት ከምትሰራባቸው ዘርፎች መካከል የፀሐይ ኃይል ልማት ግንባር ቀደም ድርሻ ከሚሰጣቸው አንዱ መሆኑ ይታወቃል። 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም