ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ፆታዊ ጥቃቶችን ለመከላከል በቅንጅት ይሰራል

ሠመራ፣ ነሐሴ 14/2017(ኢዜአ)፡- ፆታዊ  ጥቃቶችን ለመከላከል በቅንጅት እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ገለፀ።

የኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር ከአፋር ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጋር በመተባበር ለፖሊስና ፍትህ አካላት የግንዛቤ ማስጨበጫ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በዕለቱ የተገኙት በኢትዮጵያ ሚድዋይፎች ማህበር የፕሮጀክት አስተባባሪ ሲስተር ታጫውት ሳልልህ  እንደተናገሩት ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከልና ለማስቆም በቅንጅት ይሰራል።


 

ሴቶች የሚደርሰባቸውን ጥቃቶች ለህግ ከማቅረብ ባሻገር ጉዳቱን  ለመከላከል  ትኩረት መደረጉን  ነው የተናገሩት።

መድረኩም  የሴቶችን ጥቃት ለመከላከል  ግንዛቤ ማሳደግ ላይ በቅንጅት  ይበልጥ ለመስራት ማለሙን  ገልፀዋል።

ዛሬም የሴቶች ጥቃት  መኖሩን ጠቅሰው ማህበሩ ላለፉት 32 ዓመታት ባከናወናቸው ተግባራት የእናቶችና ህፃናትን  ጉዳት መቀነስና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲቀንሱ የራሱን አስተዋፅኦ ማድረጉን እስታውቀዋል።

የሴቶችን ጥቃት ለመቀነስና ለመከላከል የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወናቸው የተሻለ ግንዛቤ መፈጠሩን ገልፀዋል ።

በአፋር ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የሴቶች ተሳትፎና ንቅናቄ ዳይሬክተር ወይዘሮ ፋጡማ ሐንፈሬ በበኩላቸው እንደተናገሩት በክልሉ የሴቶችን ጥቃት የመከላከል ስራዎች እየተሰሩ ነው።


 

ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለመከላከልም ከፖሊስ፣ ከዐቃቤ ህግና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ጥምረት መኖሩን ጠቅሰው በየ 15 ቀንም በክላስተር በመገናኘት የመከላከል ስራዎችን የሚያጤን ሥራ ይሰራል ብለዋል።

በምክክር መድረኩ ከፖሊስ፣ ከፍትህ ቢሮ እና ከሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ  ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም