ቀጥታ፡

በድሬዳዋ አስተዳደር በ38 ሚሊዮን ብር የተገነቡ ዘመናዊ ቤቶች ተመርቀው ለአቅመ ደካማ ወገኖች ተላለፉ

ድሬዳዋ፤ነሐሴ 14/2017(ኢዜአ)፦በድሬዳዋ አስተዳደር በ38 ሚሊዮን ብር የተገነቡ ዘመናዊ ቤቶች ተመርቀው ለአቅመ ደካማ ወገኖች ተላለፉ።

"ሃቢታት ፎር ሂዩማኒቲ" በድሬዳዋ ከተማ በ38 ሚሊዮን ብር ያስገነባቸው 28 ዘመናዊ ቤቶች ዛሬ ተመርቀው ለአቅመ ደካማ ቤተሰቦች ተሰጥተዋል።

በድሬዳዋ መልካጀብዱ ወረዳ የተገነቡትን ቤቶች መርቀው ቁልፉን ያስረከቡት የድሬዳዋ አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ፣ የ'ሀቢታት ፎር ሂዩማኒቲ' ዓለም አቀፍ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር ጆናታን ሬክፎርድ እና ሌሎች አመራሮች ናቸው።

ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን በመተግበር የነዋሪውን ማህበራዊ ችግሮች የማቃለል ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉም ተናግረዋል።

አያይዘውም፥ መንግሥት ከባለሀብቶች፣ ከህብረተሰቡና ከግብር ሰናይ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ሰው ተኮር የልማት ሥራዎችን በትኩረት እያከናወነ ይገኛል።

በድሬዳዋ እየተከናወኑ የሚገኙት እነዚሁ የልማት ሥራዎች በተለይም የአቅመ ደካማውን ህብረተሰብ ማህበራዊ ችግሮች በከፍተኛ ደረጃ እያቃለሉ ይገኛሉ ብለዋል።

ከ'ሃቢታት ፎር ሂዩማኒቲ' ጋር በመተባበር የተገነቡትና ዛሬ ርክክብ የተደረገባቸው ቤቶችም የዚሁ ጥረት ማሳያ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ ድርጅቱ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የ'ሃቢታት ፎር ሂዩማኒቲ' ዓለምአቀፍ ድርጅት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሚስተር ጆናታን ሬክፎርድ በበኩላቸው፥ ድርጅቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ ከ62 ሚሊዮን በላይ ህዝብን ተደራሽ ያደረጉ የተለያዩ የልማት ስራዎች ማከናወኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያም 800 ሺህ ዜጎችን የልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውሰው፥ ዛሬ በድሬዳዋ የተመረቁት የአቅመ ደካማ ቤቶች ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።

ቤት የሁሉም ነገሮች መነሻና መሠረት መሆኑን ጠቅሰው፥ ድርጅቱ በድሬዳዋ ገንብቶ ያገኘውን ተሞክሮ በሌሎች የአገሪቷ አካባቢዎችም ለማስፋፋት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በድሬዳዋ በ38 ሚሊዮን ብር የተገነቡት 28 ዘመናዊ ቤቶች በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ በፍጥነትና በጥራት የተጠናቀቁ መሆናቸውን የገለፁት ደግሞ የ'ሃቢታት ፎር ሂዩማኒቲ' የኢትዮጵያ የፕሮግራም ዳይሬክተር አቶ ዓለም ሹምዬ ናቸው።

አቶ ዓለም እንዳሉት ቤቶቹ ለማህበራዊ ችግሮች ለተጋለጡ 28 ቤተሰቦች መከፋፈሉን ገልፀው፣ ለመኖሪያ ቤቶቹ ሌሎች የመሠረተ ልማቶች መሟላቱን ተናግረዋል።

በቀጣይም የቤት ባለቤት ለሆኑ ሰዎች ከሚመለከታቸው የድሬዳዋ ተቋማት ጋር በመቀናጀትና ስልጠና በመስጠት ዘላቂ ኑሮ እንዲመሰርቱ ይሰራል ብለዋል።

ዛሬ የቤት ባለቤት የሆኑት ነዋሪዎች በበኩላቸው፥ መንግስትና ድርጅቶች ተቀናጅተው የዘመናት ጥያቄያቸውን ስለፈቱላቸው ደስታና ምስጋናቸውን ገልፀዋል።

ወይዘሮ አሻ መሐመድ እንዳሉት እኔና ባለቤቴ ከልጆቻችን ጋር የማይሆን ቦታ ተጠልለን በስቃይ እንኖር ነበር፤ አሁን ባገኘነው ቤት ደስተኛ ህይወት እንመራለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም