በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ደረጃውን የጠበቀ በደንበኞች ተመራጭ የፈጣን መልዕክት አገልግሎት እየሰጠን ነው-የኢትዮጵያ ፖስታ - ኢዜአ አማርኛ
በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ደረጃውን የጠበቀ በደንበኞች ተመራጭ የፈጣን መልዕክት አገልግሎት እየሰጠን ነው-የኢትዮጵያ ፖስታ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2017(ኢዜአ)፦ ከለውጡ በኋላ በዓለም አቀፍ መመዘኛዎች ደረጃውን የጠበቀና በደንበኞች ዘንድ ተመራጭ የፈጣን መልዕክት አገልግሎት /EMS/ እየተሰጠ መሆኑን የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳግማዊ ኃይልዬ ገለጹ፡፡
በመንግስትና ፋይናንስ አገልግሎቶች፣ኢ ኮሜርስ እና በልዩ የጅምላ ሎጂስቲክስ /Bulk logistics/ ጎልቶ ለመውጣት ስትራቴጂ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ነው የተገለጸው።
የኢትዮጵያ ፖስታ ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በማከናወን የአገልግሎት አሰጣጡን ማዘመን፣ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪና ትርፋማ ተቋም መሆን ጀምሯል፡፡
ለዚህ ደግሞ ተቋሙ ውስጣዊ አሰራሩን እንዲያጠናክር እና እንዲያሻሽል መንግስት ለዘርፉ ትኩረት እንዲሰጥ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ዳግማዊ ኃይልዬ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ፖስታ ከለውጡ በፊት አንጋፋነቱን በማይመጥን ደረጃ ላይ ቆይቶ ነበር፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የፖስታ አገልግሎት ድርጅቶች ራሳቸውን እያዘመኑ ተጽዕኖ ፈጣሪነታቸውና ለማህበረሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት እሴት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ ከዓለም አቀፍ የፖስታ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር ሲነፃፀር ዝቅ ያለ እንደነበር አስታውሰው፤ ይሄንን በዘላቂነት ለመቀየር ሁሉን አቀፍ ሪፎርም መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በዚህም የውስጥ አሰራሮችን በማሻሻል፣የአገልግሎት አሰጣጡን በዓይነትና በጥራት በማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማዘመን በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያስገኙለትን ውጤቶች ማስመዝገቡን ገልጸዋል፡፡
ከለውጡ በፊት በፈጣን መልዕክት አገልግሎት ከዓለም 117ኛ ደረጃ እንደነበር አስታውሰው፥ ሪፎርሙ ከዓለም ምርጥ የፖስታ አገልግሎት ድርጅቶች አንዱ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ በዓለም የፈጣን መልዕክት አገልግሎት መመዘኛ ከጊዜ ወደ ጊዜ አገልግሎቱ እየተሻሻለ በመምጣቱ ብዙ ደንበኞች ያሉት ተመራጭ አገልግሎት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ ሰባት ዓይነት አገልግሎቶችን በጥራት፣ በፍጥነትና በተመጣጣኝ ዋጋ እየሰጠ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈፃሚው፤ በቀጣይ በመንግስትና በፋይናንስ አገልግሎት፣ በኢ ኮሜርስ እንዲሁም በጅምላ ሎጂስቲክስ ተመራጭ መሆን የሚያስችለውን እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ከኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ለምርቶቻቸው ለውጭ ገበያ ትስስር እንዲያገኙ የሎጂስቲክስ አጋር ሆኖ እንደሚሰራ ተናግርዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ብዙ እያገዘን ያለ ኩራታችን ነው ያለት አቶ ዳግማዊ፥ እንደ አፍሪካ ትልቅ የኢ ኮሜርስ መንቀሳቀሻ ማዕከል ለማድረግ በጋራ እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
መንግስት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን በጀመራቸው እንደ መሶብ የአንድ ማዕከል ላይ በመግባት ለማህበረሰቡ የተቀላጠፈ የፖስታ አገልግሎት በስፋት እሰጠን ነው ብለዋል፡፡
የፋይናንስ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ከአንድ ሺህ በላይ በሆኑ የኢትዮጵያ ፖስታ የአገልግሎት መስጫ ቅርንጫፎቹ ተጠቅመው አገልግሎት መስጠት የሚችሉበትን እድል ፈጥሯል፤ የገጠሩን ማህበረሰብ ተደራሽ ለማድረግ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡