በክልሉ በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ የቡና እና የፍራፍሬ ችግኝ ተተክሏል

ባሕርዳር፤ነሐሴ 14/2017 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 17ሺህ 650 ሄክታር መሬት ላይ የቡና እና የፍራፍሬ ችግኝ በመትከል እየለማ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

በቢሮው የአትክልትና ፍራፍሬ ባለሙያ አቶ አወቀ ዘላለም ለኢዜአ እንደገለጹት፥ በክልሉ የቡና እና የፍራፍሬ ልማትን በማስፋፋት የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በዚህም በተያዘው ክረምት 17 ሺህ 650 ሄክታር መሬት ላይ የቡና፣ የተለያየ የቆላ እና የደጋ ፍራፍሬ ችግኝ በመትከል እየለማ መሆኑን ገልጸዋል።

ከተተከለው ችግኝ ውስጥም ከቡና ሌላ አቦካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ ሙዝ፣ ዘይቱን፣ ሎሚ፣ አፕል እና ኮክ እንደሚገኝበት ጠቅሰዋል።

ተከላው የተካሄደው 354 ሺህ 841 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ መሆኑን ጠቁመው፤ የተተከለው ችግኝ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ብልጫ አለው ብለዋል።

በዘንድሮው የችግኝ ተከላ ለፍራፍሬ ልማት ምቹ መሆናቸው በተለዩ 36 ወረዳዎች በኩታ ገጠም መካሄዱን አንስተው፤ ይህም ተባይና አረምን በጋራ በመከላከል ምርታማነትን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።

በምዕራብ ጎጃም ዞን የጃቢጠህናን ወረዳ አርሶ አደር ተፈራ መልስ በሰጡት አስተያየት፤ ዝርያው የተሻሻለ የቡና ችግኝ በአንድ ሄክታር ተኩል መሬት ተክለው እያለሙ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም እስከ ሶስት ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ምርት የሚሰጥ መሆኑን ያመለከቱት አርሶ አደሩ፤ ችግኙን መንከባከብና ያረጀውን ጎንድለው በማደስ የተሻለ ምርት በመሰብሰብ ተጠቃሚ ለመሆን በባለሙያ ታግዘው እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ውበት ተስፌ፤ቀደም ሲል በሩብ ሄክታር ካለሙት የቡና ተክል ያገኙት ምርት ሸጠው ተጠቃሚ መሆናቸውን አውስተዋል።

ያገኙትን ለማስፋትም በተያዘው ክረምት ተጨማሪ የቡና ችግኝ አዘጋጅተው እየተከሉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በአንድ ሄክታር መሬት እያከናወኑት ያለው የቡና፣ አቦካዶና ማንጎ ልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን የገለጹት ደግሞ በሰሜን ጎጃም ዞን የሰሜን ሜጫ ወረዳ አርሶ አደር ነጋ ታደለ ናቸው።

ከግብርና ቢሮው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤በአማራ ክልል ከ91 ሺህ 600 ሄክታር በላይ መሬት በቡናና ፍራፍሬ ተክል ለምቶ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም