ችግሮችን በምክክር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ምሁራን ተሳትፏቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸውል- ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ችግሮችን በምክክር ለመፍታት በሚደረገው ጥረት ምሁራን ተሳትፏቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸውል- ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)

ባሕርዳር፤ ነሐሴ 14/2017(ኢዜአ)፡- ችግሮችን በምክክር በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት ምሁራን ተሳትፏቸውን ይበልጥ አጠናክረው ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) ገለጹ።
ኮሚሽኑ በአማራ ክልል ከሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ጋር በምክክሩ አስፈላጊነት፣ እስካሁን በተገኙ ስኬቶችና በቀጣይ ስራዎች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በባሕር ዳር ከተማ እያካሄደ ነው።
በመድረኩ ላይ ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) እንደተናገሩት፤ ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት ምክክርን ባህል በማድረግ ችግሮችን በጋራ መፍታት ያስፈልጋል።
ለዚህም በሃገራዊ ምክክር የሚስተዋሉ ችግሮችን በመፍታት ህዝቡ በአብሮነት፣ በፍቅርና በመተሳሰብ እንዲኖር የሚያስችል ምዕራፍ መከፈቱን ገልጸዋል።
ችግሮችን በምክክር መፍታት በሚደረገው ጥረት ምሁራን በእውቀት የታገዙ ምርምሮችን በማካሄድና የሌሎች ሀገራትን ተሞክሮ በማምጣት ተሳትፏቸውን ይበልጥ አጠናከረው ሚናቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው።
ምሁራን በሀገራችን ዘላቂ ሰላምን በማስፈን ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት የምትችሉትን ሁሉ ማበርከት አለባችሁ ብለዋል።
አባቶቻችን በየዘመናቱ ባካሄዱት ተጋድሎ ዳር ድንበሯ የተከበረ ሀገር አስረክበውናል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ሰላሟ የሰፈነና ያደገች ሀገር እንድትኖረን ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ምሁራን በምክክሩ ያልተሳተፉ ወገኖችን በማግኘት የምክክር ኮሚሽኑን ዓላማ በማስረዳት የመፍትሄው አካል እንዲሆኑ የማስቻል ስራ ማከናወን እንዳለባቸውም አንስተዋል።
የውይይት መድረኩ ከዛሬ ጀምሮ ለሁለት ቀናት እንደሚቆይ ተመልክቷል።