ቀጥታ፡

የአስተዳደር ፍርድ ቤቱ ከካፒታል ገበያ ጋር በተያያዘ ለሚቀርቡለት አቤቱታዎች ፈጣን ውሳኔ ለመስጠት ተዘጋጅቷል

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 14/2017(ኢዜአ)፦የካፒታል ገበያ አስተዳደር ፍርድ ቤት ከካፒታል ገበያ ጋር በተያያዘ ለሚቀርቡለት ቅሬታዎች እና አቤቱታዎች ፈጣን ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችለውን የሰነድ ዝግጅት ማጠናቀቁን አስታወቀ፡።

ቀልጣፋ የፋይናንስ አሠራር፣ የተሻለ የቁጠባ አቅም፣ ሰፊ የኢንቨስትመንት ዕድልና ፍትሃዊ የኃብት ክፍፍል ለመፍጠር የካፒታል ገበያ በአዋጅ ቁጥር 1248/2013 መቋቋሙ ይታወቃል፡፡

ይህንን ተከትሎ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን፣ ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ እንዲሁም የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት መቋቋማቸውም ይታወሳል፡፡

የካፒታል ገበያ አስተዳደራዊ ፍርድ ቤት ሰብሳቢ ዳኛ አብነት ዘርፉ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በካፒታል ገበያ ስርዓት በርካታ ባለድርሻ አካላት የሚሳተፉበት ነው፡፡

በዚህ ሂደት ቅሬታዎች አቤቱታዎች ሊቀርቡ የሚችሉ መሆኑን አንስተው አስተዳደራዊ ፍርድ ቤቱ በካፒታል ገበያው የሚቀርቡ ቅሬታዎችን እና አቤቱታዎችን ለመፍታት መቋቋሙን አስታውቀዋል፡፡

አስተዳደር ፍርድ ቤቱ በኢትየጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣንና በሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ በሚወሰኑ ውሳኔዎች ላይ ቅሬታ ያላቸው አካላት የሚያቀርቡትን ቅሬታ መርምሮ ውሳኔ የሚሰጥ መሆኑን አስታውቀዋል፡።

ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን እንዲሁም ሰነደ ሙዓለ ንዋይ ገበያ ስራ መጀመራቸውን ተከትሎ ወደ ስራ መግባቱን አንስተዋል፡፡

ተቋሙ ስራ ለመጀመር የሚያስችሉ ተግባራት ሲያከናውን የቆየ ሲሆን የአደረጃጀት ስራዎቹን በውጤታማነት ማጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ከካፒታል ገበያው ጋር በተያያዘ የሚቀርቡ ማንኛውንም ቅሬታዎች በመመልከት የይግባኝ ውሳኔ ለመስጠት በሚያስችል ቁመና ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከካፒታል ገበያው ጋር ተያይዞ ለሚቀርቡ ቅሬታዎችና እና ይግባኞች ፈጣን ውሳኔ ለመስጠት የሚያስችለውን የተለየ የዳኝነት ስራ የሚመራበት ሰነድ (role of procedure) ማጠናቀቁንም አስታውቀዋል፡።

ሰነዱ ከመደበኛው ዳኝነት በተለየ መልኩ ለፍርድ ቤቱ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በተፋጠነ መንገድ ውሳኔ መስጠት የሚያስችል መሆኑን አንስተዋል።

የካፒታል ገበያው አዲስ በመሆኑ ህብረተሰቡ በቂ መረጃ እንዲኖረው እንዲሁም ለህግ ባለሙያዎች በቂ ግንዛቤ የሚሰጥ መግለጫ መጽሐፍ (ጋይድ ቡክ) መዘጋጀቱንም አስታውቀዋል።

ባለጉዳዮች ወደ ተቋሙ በአካል ሳይመጡ ጉዳያቸውን እንዲያቀርቡ እና እንዲከታተሉ የሚያስችል የዲጂታል ቴክኖሎጂ ግንባታ በትኩረት እየተሰራበት መሆኑንም ሰብሳቢው ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም