አርቲስት ደበበ እሸቱ ሀገር ወዳድነትን በማስረጽ ኢትዮጵያዊነትን አቀንቅኖ ያለፈ ታላቅ የሙያ አባት ነው - የሙያ አጋሮቹ

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 13/2017(ኢዜአ)፦ አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ሀገር ወዳድነትን በማስረጽ ኢትዮጵያዊነትን አቀንቅኖ ያለፈ ታላቅ የሙያ አባት ነው ሲሉ የሙያ አጋሮቹ ገለጹ። 

የአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ሥርዓተ ቀብር ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሙያ አጋሮቹና ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

በ1934 ዓ.ም የተወለደው አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከ1943 ዓ.ም እስከ 1950 ዓ.ም ድረስ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትሏል። 

ከ1950 ዓ.ም እስከ 1951 ዓ.ም ድረስም በኢትዮጵያ አየር ኃይል ፓይለት ማሰልጠኛ፤ ከ1951 ዓ.ም እስከ 1953 ዓ.ም በደብረ ብርሃን መምህራን ኮሌጅ ትውልድ የማነጽ የመምህርነት ትምህርት ጥበብን ቀስሟል።

በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የትምህርት ተቋማት ትምህርቱን የተከታተለው ጉምቱው አርቲስት የበጎ አድራጎትና ሰብዓዊ አገልግሎት ስራም መገለጫዎቹ እንደነበሩ የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል።

የጥበብ አጋሩ አንጋፋው አርቲስት አበበ ባልቻ እንደሚናገረው፤ አርቲስት ደበበ እሸቱ ከሙያ አጋሩ ወጋየሁ ንጋቱ ጋር በመሆን የኢትዮጵያን የኪነ-ጥበብ ታሪክ በወሳኝ ምዕራፍ ማሸጋገር የቻለ አንጋፋ የጥበብ ሰው ነበር ብሏል።

ከኪነ-ጥበብ ስራዎቹ ባለፈም ለብዙዎች በአርዓያነት የሚወሰድ የመልካም ስብዕና መገለጫ የሆነ ደግና በስራ ትጋት የተገነባ ጠንካራ ሰው እንደነበር ገልጿል።


 

ሌላኛው የሙያ አጋር አርቲስት ደበሽ ተመስገን በበኩሉ፤ ጋሽ ደቤ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የኪነ-ጥበብ ታሪክ ውስጥ ቀዳሚና ጉምቱ ከሚባሉ የጥበብ አባቶች ውስጥ ግንባር ቀደሙ ነበር ብሏል።

በኪነ-ጥበብ ስራውም ከሀገር ውስጥ በተጨማሪ በአህጉረ አፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር የገዘፈ ስምና ዝናን የያዘ  ኢትዮጵያዊያን የሚኮሩበት ታላቅ አባት እንደነበርም ገልጿል። 

አርቲስት ሙሉዓለም ታደሰ በበኩሏ፤ አርቲስት ደበበ ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ በትልልቅ መድረኮች የሚሰራበትን ዕድል በማመቻቸት ትልቅ የሙያ አባታችን ነበር ብላለች። 


 

በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃም ዘመን ተሻጋሪ ታላላቅ ስራዎች ሰርቶ ያለፈ የጥበብ አውራ እንደነበር ገልፃለች።

አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ፤ አርቲስት ደበበ እሸቱም ከኪነጥበብ ሙያ ባለፈ ሰው አካባሪነትን፣ ቅንነትና ታታሪነትን አስተምሮ ያለፈ በርካታ ጸጋዎችን የታደለ አባት እንደነበርም ገልጿል።


 

የአንጋፋው የጥበብ ሰው የስራ ውጤቶችም የተገነባበትን ስብዕና በግልጽ በማሳየት ሀገር ወዳድነትን በማስረጽ ኢትዮጵዊነትን የሚያቀነቅኑ መሆናቸውን ተናግሯል።

የአርቲስት ደበበ እሸቱ ስራዎች ከሀገር ውስጥ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ ጭምር የናኙ መሆናቸውን  የተናገረው  ደግሞ አርቲስት ሰለሞን ታሼ (ጋጋ)  ነው።


 

አንጋፋው አርቲስት በህይወት ዘመኑ ለሀገሩና ወገኑ ካበረከታቸው ዘርፈ ብዙ የኪነ-ጥብብና ሌሎች ስራዎች በተጨማሪም ከህልፈቱ በኋላም የዐይን ብሌኑን ለግሶ ያለፈ የሀገር ባለውለታ መሆኑን ተናግሯል።

ሁለገቡ የጥበብ ሰው በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ በማገልገል ላበረከተው ጉልህ አስተዋጽኦ በሐምሌ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተበርክቶለታል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እጅም "ኢትዮጵያን ስላገለገሉ ኢትዮጵያ ታመሠግናለች" በሚል መሪ ሃሳብ በተሰናዳው ሀገራዊ ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያን ከፍተኛ የክብር ሜዳይ ተበርክቶለታል።

የገዘፈ ሰብዓዊ እና ኪናዊ ግብርን የከወነው የጥበብ አርበኛ ደበበ እሸቱ ባጋጠው የጤና እክል በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በተወለደ በ83 ዓመቱ ነሐሴ 11 ቀን 2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

በሥርዓተ ቀብሩ ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር)፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ የሙያ አጋሮቹና ወዳጅ ዘመዶቹ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም