የአካባቢያችንን ሰላም በዘላቂነት በማስጠበቅ ልማትን ለማፋጠን ተሳትፏችንን እናጠናክራለን -በኢሉአባበር ዞን ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአካባቢያችንን ሰላም በዘላቂነት በማስጠበቅ ልማትን ለማፋጠን ተሳትፏችንን እናጠናክራለን -በኢሉአባበር ዞን ነዋሪዎች

መቱ፤ ነሐሴ 13/2017 (ኢዜአ)፡- የአካባቢያቸውን ሰላም በዘላቂነት አስጠብቆ በማስቀጠል ልማትን ለማፋጠን ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በኢሉአባበር ዞን ነዋሪዎች ገለጹ።
ከዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የተውጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ የሰላምና ልማት ኮንፈረንስ በመቱ ከተማ ተካሂዷል።
የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ በዞኑ ሰላምን አፅንቶ ለማስቀጠል የፀጥታ አስከባሪ አካላትን በመደገፍ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።
የተጀመሩ አዳዲስ የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉም እያገዙ መሆኑን አመልክተዋል።
ከተሳታፊዎቹ ወስጥ አቶ በንቲ ጂማ፣ ለየትኛው ልማት ስራ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፤ በየአካበቢያቸው ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት ሰላማቸውን እየጠበቁ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሌላው አቶ ደጀኔ ከበደም በበኩላቸው፤ ሰላምን ማስከበር በጸጥታ አካላት ብቻ ባለመሆኑ ተደራጅተው ሰላማቸውን ለማፅናት በትብብር እየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የአካባቢያቸውን ሰላም በዘላቂነት አፅንቶ በማስቀጠል ልማትን ለማፋጠን ሲያዳርጉ የቆዩትን ተሳትፎ እንደሚያጠናክሩ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንዳልካቸው ተፈሪ ፤ በዞኑ በተለይ በግብርናው ዘርፍ እየተተገበሩ በሚገኙ ኢኒሼቲቮች አበረታች ውጤቶች እያስመዘገቡ ነው ብለዋል።
በሁሉም ዘርፎች የተጀመሩትን ልማቶች በማጠናከር ወደተሻለ ምዕራፍ ለመሸጋገርም ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የተጀመረውን የልማት ስራ የበለጠ ለማፋጠን ሰላም ዋነኛና ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ የዞኑ ነዋሪዎች ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።