አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ዝግጅት ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ አደረገ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 13/2017(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከግብፅ እና ሴራሊዮን ጋር ለሚያከናውናቸው የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ 7ኛ እና 8ኛ ጨዋታዎች ዝግጅት አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለ26 ተጫዋቾች ጥሪ አድርገዋል።
አቡበከር ኑራ፣ ቢኒያም ገነቱ እና ፍሬው ጌታሁን ስብስብ ውስጥ ግብ ጠባቂዎች ናቸው።
አስራት ቶንጆ፣ ያሬድ ካሳዬ፣ ረመዳን የሱፍ፣ ራምኬል ጀምስ፣ ሱሌይማን ሃሚድ፣አህመድ ረሺድ፣ ምኞት ደበበ፣ ያሬድ ባየህ እና ንጋቱ ገብረስላሴ በተከላካይ መስመር ላይ ጥሪ ተደርጎላቸዋል።
ሀብታሙ ተከስተ፣ ሃይደር ሸረፋ፣ በረከት ወልዴ፣ አብዱልከሪም ወርቁ፣ ከነዓን ማርክነህ፣ ቢኒያም በላይ እና ወገኔ ገዛኸኝ በአማካይ ክፍል ላይ እንደተጠሩ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል።
በአጥቂ መስመር ቸርነት ጉግሳ፣ በረከት ደስታ፣ ኪቲካ ጅማ፣ ዳዋ ሆቴሳ፣ አህመድ ሁሴን፣ መሐመድ አበራ እና ቢኒያም አይተን እና አህመድ ሁሴን ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።
ጥሪ የተደረገላቸው ተጫዋቾች እስከ ነገ እንዲሰባሰቡ ጥሪ የተላለፈ ሲሆን ተጫዋቾቹ በቀጣይ ቀናት ወደ አዳማ በማምራት ዝግጅታቸውን እንደሚጀምሩ ገልጿል።
ኢትዮጵያ ነሐሴ 30 ቀን 2017 ዓ.ም ከግብጽ ጋር በካይሮ፣ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም ከሴራሊዮን ጋር በሞኖሮቪያ የማጣሪያ ጨዋታዋን ታደርጋለች።
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እ.አ.አ በ2026 በአሜሪካ፣ ካናዳ እና ሜክሲኮ የጣምራ አዘጋጅነት ለሚካሄደው 23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ማጣሪያ በምድብ አንድ ከግብጽ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ሴራሊዮን፣ ጊኒ ቢሳው እና ጅቡቲ ተደልድሎ እስከ አሁን ስድስት ጨዋታዎችን አድርጓል።
ብሄራዊ ቡድኑ በስድስት ነጥብ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
ኢትዮጵያ በምድቡ ካደረገቻቸው ጨዋታዎች መካከል ጅቡቲን ሞሮኮ ላይ 6 ለ 1 የረታችበት ጨዋታ ተጠቃሽ ነው።