ቀጥታ፡

ኮሚሽኑ በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞች ቤቶች ግንባታ እና እድሳት አስጀመረ

አምቦ፤ ነሐሴ 13/2017(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በምዕራብ ሸዋ ዞን የአቅመ ደካሞች ቤቶች ግንባታ እና እድሳት አስጀመረ።

የአረጋውያን ቤት እድሳት እና ግንባታው በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጀርሳ ላፎ እና ደንዲ ወረዳዎች ሲሆን ለዚህም 20 ሚሊየን ብር መበጀቱ ተገልጿል።

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንዳሉት ከሚሽኑ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እየተሳተፈ ነው።


 

ኮሚሽኑ ባለፉት ዓመታትም በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተለያዩ ክልሎች የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞችን ቤት እድሳት እና ግንባታ ሲያካሄድ መቆየቱን ገልጸዋል።

በተያዘው ክረምትም በምዕራብ ሸዋ ዞን ኤጀርሳ ላፎ እና ደንዲ ወረዳዎች በ20 ሚሊየን ብር የአቅመ ደካሞች ቤቶች ግንባታ ማስጀመሩን ተናግረዋል።

የምዕራብ ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዲዳ ጉደታ በበኩላቸው በዞኑ ሁሉም ወረዳዎች የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ባለድርሻ አካላትን ባሳተፈ መልኩ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።


 

በበጎ ፈቃድ አገልግሎቱም የአረጋውያንና የአቅመ ደካሞች ቤት ግንባታ እና እድሳት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በደም ልጋሳ፣ በቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ግንባታና በተለያዩ ዘርፎች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ክረምቱ ከገባ ጀምሮ እነዚህ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች በተጠናከረ መልኩ እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸው አሁንም ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል ነው ያሉት።


 

ቤት እድሳት የተጀመረላቸው ወይዘሮ አርፋሴ ፊጣ፤ ከስድስት ልጆቻቸው ጋር ሊወድቅ የደረሰ ቤት ውስጥ እየኖሩ ለብዙ ችግር ተጋልጠው መቆየታቸውን ተናግረዋል።

አሁን ላይ ቤታቸው እድሳት በመጀመሩ መደሰታቸውን ገልጸው በተደረገላቸው ድጋፍ በጎ ፈቃደኞችን አመስግነዋል።


 

ሌላዋ የቤት እድሳት ከተጀመረላቸው ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ሌንሴ ደበሌ፣ ከአቅም ማነስ ምክንያት ለብዙ አመታት በጣም ያረጀ ቤት ውስጥ በመኖር ለዝናብና ብርድ መጋለጣቸውን ተናግረዋል።

አሁን ላይ የቤታቸው እድሳት በመጀመሩ እጅግ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም