ዩኒቨርሲቲው የ"ሞሪንጋ" ተክል ምርት ላይ እሴት በመጨመር የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ፕሮጀክት ቀርፆ ወደ ተግባር ገብቷል - ኢዜአ አማርኛ
ዩኒቨርሲቲው የ"ሞሪንጋ" ተክል ምርት ላይ እሴት በመጨመር የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ፕሮጀክት ቀርፆ ወደ ተግባር ገብቷል

አርባምንጭ፤ነሐሴ 13/2017 (ኢዜአ)፡-አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የ" ሞሪንጋ" ተክል ምርት ላይ እሴት በመጨመር የውጭ ምንዛሪ ማስገኘት የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርፆ ወደ ተግባር መግባቱን አስታወቀ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጋሞና ወላይታ ዞኖች በ90 ሄክታር መሬት ላይ የሞሪንጋ ችግኝ ተከላ ለማከናወን ስራ ዛሬ ተጀምሯል።
በመረሃ ግብሩ ላይ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አብደላ ከማል(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደናገሩት፥ በጋሞ እና ወላይታ ዞኖች በሚገኙ ሦስት ወረዳዎች የሞሪንጋ ምርትን እሴት በመጨመር የውጭ ምንዛሪ ማግኘት የሚያስችል ፕሮጀክት ተቀርጾ ወደ ተግባር ተገብቷል።
ለዚህም ከተለያዩ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ድርጅቶች ጋር በትብብር እየተሠራ ይገኛል ብለዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰፊ የሞሪንጋ አቅም መኖሩን ጠቅሰው፥ዩኒቨርሲቲው ይህን አቅም በምርምር በማበልጸግ እሴት ተጨምሮበት ለሀገር ውስጥና ለውጪ ገበያ እንዲቀርብ እያመቻቸ መሆኑን ገልጸዋል።
የሞሪንጋ ፕሮጀክቱ እሴት በመጨመር የሕብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማሳደግ ባሻገር ለአረንጓዴ አሻራ ራዕይ ስኬት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቁመዋል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ተክሉ ወጋየሁ በበኩላቸው፤ በሞሪንጋ ፕሮጀክቱ የችግኝ ተከላ መረሃ ግብር በጋሞ ዞን ምዕራብ አባያ ወረዳ ፤በወላይታ ዞን ደግሞ አባላ አባያና ኪንዶ ኮይሻ ወረዳዎች ውስጥ በ90 ሄክታር መሬት ላይ እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ለአንድ ዓመት የሚቆየው ፕሮጀክቱ የሞሪንጋ ተክል ልማት ሂደት ከ20 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
ፕሮጀክቱ ተግባራዊ በሆኑባቸው አከባቢዎች የማቀነባበሪያ ፋብሪካ እንደሚገነባና በዘርፉ የተሠማሩ በርካታ ማህበራት ተጠቃሚ እንደሚሆኑ አስረድተዋል።
ዩኒቨርሲቲው ለፕሮጀክቱ ማስፈጸሚያ ድጋፍ መገኘቱን የገለጹት ደግሞ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አዲሱ ፈቃዱ(ዶ/ር) ናቸው።
በጋሞ እና ወላይታ ዞኖች የተጀመረው የሞሪንጋ ፕሮጀክት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ጠቁመዋል።
የሞሪንጋ ምርቱ እሴት ተጨምሮበት የተለያዩ መድሃኒቶች፣ መዋቢያና የምግብ ዘይት በማምረት ከውጭ የሚገባውን ከመተካት ባለፈ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማሳደግ ያለው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን ገልጸዋል።