ቀጥታ፡

የሁለገቡ የጥበብ ሰው አርቲስት ደበበ እሸቱ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 13/2017 (ኢዜአ)፡-የሁለገቡ የጥበብ ሰው አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ሥርዓተ ቀብር በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል።

በ1933 ዓ.ም የተወለደው አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ የመጀመሪያና 2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ከ1943 ዓ.ም እስከ 1950 ዓ.ም ድረስ በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ተከታትሏል።

በመቀጠልም ከ1950 ዓ.ም እስከ 1951 ዓ.ም ድረስ ባሉት ዓመታት በኢትዮጵያ አየር ኃይል ፓይለት ማሰልጠኛ የተከታተለ ሲሆን ከ1951 ዓ.ም እስከ 1953 ዓ.ም በነበሩት ዓመታትም በደብረ ብርሃን መምህራን ኮሌጅ የመምህርነት ትምህርቱን በመከታተል ትውልድ የማነጽ ጥበብን ቀስሟል።

በቀድሞው ቀዳማዊ ኃለስላሴ በአሁኑ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም የኪነ-ጥበብ እውቀትና ክህሎቱን ለማሳደግ መሠረት ጥሏል።


 

የሥነ-ጥበብ ትምህርቱን ወደከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ከፍተኛ ትጋት የነበረው የጥበብ ሰው አርቲስት ደበበ በ1958 ዓ.ም ከመጀመሪያዎቹ ጥቁር ተማሪዎች አንዱ ለመሆን ከሌላኛው ታላቅ ከያኒ ወጋየሁ ንጋቱ ጋር በመሆን በሃንጋሪ ቡዳፔስት ከኢንቲቩሽ ሎራንድ የሥነ-ጥበብ ትምህርት ቤት ለምርቃት በቅቷል።

የውጭ ሀገር የሥነ-ጥበብ ትምህርቱን አጠናቆ ከተመለሰ በኋላም ከወይዘሮ አልማዝ ደጀን ጋር የትዳር ህይወቱን በመመስረት ሶስት ሴትና አንድ ወንድ ልጆችን በማፍራት ስምንት የልጅ ልጆችን ለማየት በቅቷል።

በድርሰትም የተዋናይ ዝግጅት አንድና ሁለት (ከስታንስላቭስኪ) እና የደም እንባ (ከዳዊት ወልደጊዮርጊስ) በትርጉም፤ ለሊቀመንበሩ የተፃፈ ደብዳቤ፣ ሃሞክ ቱ ብሪጅ፣ የአውደ ጥናት ውጤቶች እንዲሁም የእምነቴ ፈተና አንድና ሁለት የተሰኙ መጽሃፍትን ለተደራሲያን አቅርበዋል።

አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሽቱ ጠልፎ በኪሴ፣ ያላቻ ጋብቻ፣ ሮሚዮና ዡልየት፣ ዳንዴው ጨቡዴ፣ አንድ ዓመት ከአንድ ቀን፣እናት ዓለም ጠኑ፣ በቀይ ካባ ስውር ደባ፣ የአዛውንቶች ክበብ፣ የወፍ ጎጆ፣ ማዕበል፣ የቬኒሱ ነጋዴ፣ ዘ ጌም ኦፍ ቼዝ፣ ኦቴ በተሰኙ እና ሌሎች ከ40 በላይ ታላላቅ ተጠቃሽ የመድረክ ስራዎችን አበርክቷል።


 

ዘ-ሴይለር ፍሮም ጅብራልተር፣ሻፍት ኢን አፍሪካ፣ ጉማ እና አፍሪ በተሰኙ ፊሎሞችንም ሰርቶ፣ ዜሌዳ፣ ዘ-ግራንድ ሪቤሊዮን፣ ዘ-ገሬቭ ዲገር፣ ሬድ ሊቭስ፣ ስጋ ያጣ መንፈስ፣ ስውር ችሎት፣ ሰባ ሰላሳ፣ ትውልድና ሌሎች ፊልምችንም ሰርቷል።

አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ በሀገር ፍቅርና ብሔራዊ ቴያትር ለበርካታ ዓመታት በበጎ ፈቃድ አገልግሎትና ሰብዓዊነት፣በተዋናይና አዘጋጅነት በማገልገል በራዲዮ፣ ቴሌቪዥን፣ በፊልምና ጋዜጠኝነት የሙያ መስኮች በኮሜዲና ትወና የመድረክ ቴያትር መድረኮችን በመስራት ለበርካቶች ፋና ወጊ መሆን የቻለ የጥበብ ሰው እንደነበር የህይወት ታሪኩ ያስረዳል።

ሁለገቡ የጥበብ ሰው አርቲስት ደበበ እሸቱ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያ በማገልገል ላበረከተው ጉልህ አስተዋጽኦ በሐምሌ 13/2015 ዓ.ም አንጋፋው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ተበርክቶለታል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እጅም "ኢትዮጵያን ስላገለገሉ ኢትዮጵያ ታመሠግናለች" በሚል መሪ ሃሳብ በተሰናዳው ሀገራዊ ዝግጅት ላይ የኢትዮጵያን ከፍተኛ የክብር ሜዳይ ተበርክቶለታል።

የገዘፈ ሰብዓዊ እና ኪናዊ ግብርን የከወነው የጥበብ አርበኛ አርቲስት ደበበ እሸቱ ባጋጠው የጤና እክል በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በተወለደ በ83 ዓመቱ ነሐሴ 11/2017 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል።

በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ቅድስት ስላሴ ካቴደራል በተፈጸመው የአንጋፋው አርቲስት ሥርዓተ ቀብር ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጂጌ (ዶ/ር)፣ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ(ዶ/ር)፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪ ሚኒስትር ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፣ የሰላም ሚኒስትር መሀመድ እድሪስ፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሙያ አጋሮቹና ወዳጅ ዘመዶቹ ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም