በዞኑ ለአርሶ አደሩ በተመቻቸው አማራጭ የሃይል አቅርቦት ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪን መቆጠብ ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ለአርሶ አደሩ በተመቻቸው አማራጭ የሃይል አቅርቦት ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪን መቆጠብ ተችሏል
ደሴ፤ ነሐሴ 13/2017(ኢዜአ) ፡- በደቡብ ወሎ ዞን ለአርሶ አደሩ በተመቻቸው አማራጭ የሃይል አቅርቦት ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪን በመቆጠብ ለውጥ ማምጣት መቻሉ ተገለጸ።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በዞኑ ከ56 ሺህ በላይ አባውራና እማውራ አርሶ አደሮችን በተለያዩ የሀይል አማራጭ ቴክኖሎጅዎች ተጠቃሚ መሆናቸውን የዞኑ ውሃና ኢነርጂ ልማት መምሪያ አስታውቋል።
በዞኑ በቃሉ ወረዳ 01 ቀበሌ አርሶ አደር አህመድ ሰይድ በሰጡት አስተያየት፤ ዘንድሮ የተገነባላቸው ባዮጋዝ ለአገልግሎት በመመቻቸቱ ማገዶ ፍለጋ ያጠፉት የነበረውን ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ መቆጠብ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
ከባዮጋዙ የሚወጣውን ዝቃጭ ለማዳበሪያነት በመጠቀም የመሬት ለምነትን ለመጠበቅና ምርታማነትን ለማሳደግ አስችሎኛል ብለዋል።
ሌላዋ የኩታበር ወረዳ 03 ቀበሌ አርሶ አደር ፋጡማ አሊ ፤ ዘንድሮ የማገዶ ቆጣቢ ምድጃ ተጠቃሚ መሆናቸው ገልፀው፤ ጊዜና ጉልበታቸውን በመቆጠብ ለሌላ አገልግሎት ለማዋል ምቹ ሁኔታ እንደፈጠረላቸው ገልፀዋል።
በጭስ እየታፈኑ በዓይናቸው ላይ ይደርስ የነበረው የጤና ችግርም ማቃለሉን አንስተዋል።
የዞኑ ውሃና ኢነርጂ ልማት መምሪያ ኃላፊ ጌታቸው ጽጌ በበኩላቸው፤ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦትና በአማራጭ ኢነርጂ ዘርፎች አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመቱ የታዳሽ ሃይል ቴክኖሎጂዎችን አቅርቦት በማመቻቸት ለ56 ሺህ 300 አባውራና እማውራ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 627 የባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ግንባታ፣ 48 ሺህ 777 የተሻሻሉ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችና ስድስት ሺህ 896 በፀሃይ ሃይል የሚሰሩ የሃይል አማራጮች እንደሚገኙባቸው ጠቅሰዋል።
በዚህም ለምግብ ማብሰልና ለመብራት በሚል ይጨፈጨፍ የነበረውን ደንና በጪስ ምክንያት በሕብረተሰቡ ላይ ይደርስ የነበረውን የጤና እክል መከላከል መቻሉን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ባዮጋዝ ቴክኖሎጂ ገንብተው የሚጠቀሙ አርሶ አደሮች ተረፈ ምርቱን ለአፈር ማዳበሪያነት በመጠቀም የማዳበሪያ ወጪን በመቀነስ ምርታማነትን ለማሳደግ እያገዘ መሆኑንም አስረድተዋል።
በተያዘው የበጀት ዓመትም የተለያዩ አማራጭ የሃይል አቅርቦትን የማመቻቸቱ ተግባር አጠናክሮ በማስቀጠል ሕብረተሰቡን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
ከውሃና ኢነርጂ ልማት መምሪያው የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በደቡብ ወሎ ዞን በ2016 የበጀት ዓመት ከ35 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን የተለያየ ኃይል አማራጭ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።