የሚኤሶ-ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ለምታደርገው የንግድና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የላቀ ፋይዳ አለው

አዲስ አበባ፤ነሐሴ 13/2017 (ኢዜአ)፡-የሚኤሶ-ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ግንባታ ኢትዮጵያ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ለምታደርገው የንግድና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የላቀ ፋይዳ እንዳለው የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ገለጹ፡፡

የሚኤሶ-ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ይፋዊ ማስጀመሪያ ስነ-ስርዓት በድሬዳዋ ከተማ ተከናውኗል።


 

መንገዱ የትራንስፖርት ወጪንና የትራፊክ አደጋን የሚቀንስ መሆኑም ተገልጿል።

የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ለአገር እድገትና ብልፅግና ወሳኝ የሆነው የመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ በትኩረት እየተሰራበት ነው።

የሚኤሶ-ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ከዚህ በፊት ለመጓዝ የሚፈጀውን ከአምስት ሰዓት በላይ ጊዜ ወደ አንድ ሰዓት ተኩል መቀነስ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ የምትገኝበት የአፍሪካ ቀንድ ትስስር ኢኒሼቲቭ አካል ሲሆን አገሪቱ ከቀጣናው ሀገራት ጋር ለምታደርገው የንግድና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የላቀ ፋይዳ ያለው፣ የትራንስፖርት ወጪንና የትራፊክ አደጋን የሚቀንስ መሆኑንም ተናግረዋል።

ፕሮጀክቱ የህልማችን ነፀብራቅ፣ የመሻት ማሳያ፣ የአገር ፍቅርና ትጋት ውጤት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ ዘመናዊ፣ደህንነቱ የተጠበቀና ምቹ ትራንስፖርት ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል።


 

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በበኩላቸው፤ የመንገድ ግንባታው ጊዜን የሚቀንስ፣ አዳዲስ የኢኮኖሚ እድሎችን የሚፈጥር እንዲሁም የወጪና ገቢ ንግድን የሚያቀላጥፍ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብድራህማን፥ ፕሮጀክቱ በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ የሚገነባና 144 ኪሎ-ሜትር የሚሸፍን ነው ብለዋል።


 

መንገዱ ከአለም ባንክ በተገኘ 62 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር የሚገነባ ሲሆን ስራውን የቻይና ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽንና ሲችዋን ሮድ ኤንድ ብሪጅ በጥምረት እንደሚያከናውኑት እና በአራት አመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም