ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመኗን የሚያበስሩ አያሌ ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክቶችን ጀምራ በፍጥነትና በጥራት ታጠናቅቃለች

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 13/2017(ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመኗን የሚያበስሩ አያሌ ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክቶችን ጀምራ በፍጥነትና በጥራት ታጠናቅቃለች ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ 144 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን የሚኤሶ - ድሬዳዊ የፍጥነት መንገድ ግንባታን አስጀምረዋል።


 

በማስጀመሪያ መርኃግብሩ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊና የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ፣ የፌደራልና የክልል መንግሥታት ከፍተኛ የአመራር አባላት ተገኝተዋል።

የፍጥነት መንገዱ ከዓለም ባንክ በተገኘ 62 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር የሚገነባ ሲሆን በአራት ዓመታት እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ላለ ሀገር፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለማጎልበትና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የመንገድ መሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስት ማድረግ እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል።


 

የሚኤሶ -ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ መንግስት ትራንስፖርትን ለማዘመን ያለውን ቁርጠኝነትና የበለጸገች ኢትዮጵያን የመገንባት ራዕያችን እውን እየሆነ መምጣቱን የሚያሳይ ወሳኝ መሠረተ ልማት ነው ብለዋል።

የፍጥነት መንገዱ ሁለት ክልሎችንና የድሬዳዋ ከተማን በማስተሳሰር ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መስተጋብሮችን በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያጎለብት ተናግረዋል።

መንገዱ ለሀገር ውስጥ ምርቶች ታላላቅ የገበያ ዕድሎችን የሚፈጥርና ቀጣናዊ የነጻ የንግድ ግቦችን ከማሳካት አኳያ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል ነው ያሉት።


 

የምሥራቁ ኮሪደር የሀገራችን የገቢ እና ወጪ ንግዶች የሚሳለጡበት ትልቁ የንግድ መሥመር መሆኑን ጠቅሰው፤ ከወደብ ወደ ማዕከላዊ የሀገሪቱ ክፍል የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ወጪና ጊዜ ቆጣቢ እንዲሆኑ እንደሚያስችልም ጠቁመዋል።

የፍጥነት መንገዱ ከባቡር መሥመሩ ጋር የሚፈጥረው መስተጋብር የተሳለጠ የትራንስፖርት አማራጭ አቅርቦት እንዲኖርና የገበያ ተወዳዳሪነት እንዲያድግ ያደርጋል ነው ያሉት።

ይህ ግዙፍ የኢኮኖሚ አውታር የሆነው የሚኤሶ - ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ በታቀደለት ደረጃና ጊዜ እንዲጠናቀቅ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ አሳስበዋል።

በብልፅግና ዘመን ድንጋይ አስቀምጦ መጥፋት፣ ጀምሮ መተው፣ ከጥራት በታች ሠርቶ መመረቅ አይፈቀድም ሲሉም በአፅንኦት አንስተዋል።


 

መንግሥት ለሚኤሶ-ድሬዳዋ የፍጥነት መንገድ ፕሮጀክት መሳካት ቀን ከሌሊት ያልተቋረጠ ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

በቀጣይም የኢትዮጵያ ማንሰራራት ዘመኗን የሚያበስሩ አያሌ ታሪክ ቀያሪ ፕሮጀክቶችን እንገነባለን ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የጀመርናቸውን በፍጥነትና በጥራት እናጠናቅቃለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም