መንግስት የህፃናትን የዐይን ጤንነት በመጠበቅ የዕይታ ጉዳትን ለመቀነስ ትኩረት አድርጓል - ኢዜአ አማርኛ
መንግስት የህፃናትን የዐይን ጤንነት በመጠበቅ የዕይታ ጉዳትን ለመቀነስ ትኩረት አድርጓል
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 13/2017(ኢዜአ)፦መንግስት የህፃናትን የዐይን ጤንነት በመጠበቅ የዕይታ ጉዳትን ለመቀነስ የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን በትኩረት እያከናወነ እንደሚገኝ የጤና ሚኒስትር ዶክተር መቅደስ ዳባ ገለጹ።
የአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለህፃናት ዐይን ህክምና ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል የመጀመሪያውን የህጻናት የዐይን ሕክምና ማዕከል አስመርቋል።
በምርቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ፣ የአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሽመልስ ገዛኸኝን ጨምሮ ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር መቅደስ ዳባ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የህፃናትን የዐይን ጤንነት በመጠበቅ የዕይታ ጉዳትን ለመቀነስ በትኩረት እየተሰራ ነው።
ዛሬ የአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ማዕከል ያስመረቀው የህፃናት ዐይን ማዕከል ጥራት ያለው የስፔሻሊቲ የዐይን ሕክምና መስጠት የሚያስችል ነው ብለዋል።
ማዕከሉ የህፃናትን የዐይን አካል በመንከባከብ የዐይን ዕይታ የማጣት ችግርን ቀድሞ ለመከላከል ጉልህ ፋይዳ እንደሚኖረው ተናግረዋል።
በቀጣይም የመሰል ማዕከላት ግንባታን በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በማስፋት የአገልግሎት ጥራትና ተደራሽነትን ለማሳደግ በቁርጠኝነት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
የአለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ዋና ስራ አስኪያጅ ዶክተር ሽመልስ ገዛኸኝ በበኩላቸው፤ የህፃናት ዐይን ማዕከሉን አለርት ኮምፕሪሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ከተባባሪ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ማስገንባቱን ተናግረዋል።
ማዕከሉ የህፃናትን የህክምና አገልግሎት በማላቅ ለዐይን እንክብካቤና ወቅቱን የጠበቀ ጥራት ያለው የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት የማይተካ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።