ቀጥታ፡

ህብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ልምዱን ሊያሳድግ ይገባል - የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 13/2017(ኢዜአ)፦ ህብረተሰቡ የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ልምዱን ሊያሳድግ እንደሚገባ የንግድ እና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ ለሁለተኛ ጊዜ ያዘጋጀው የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ሳምንት ከነሐሴ 24 እስከ 29 ቀን 2017 ዓ.ም በኢትዮጵያ የጥራት መንደር ይካሄዳል።

በንግድ ሳምንቱ ላይ ከ200 በላይ የንግድ ማህበረሰብ አባላት ምርት እና አገልግሎታቸውን ያስተዋውቃሉ።

የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ስራ አስፈፃሚ አቶ ወንድሙ ፍላቴ የሁነቱ አላማ ዜጎች በሀገር ውስጥ ምርት የመኩራትና የሀገር ውስጥ ምርቶችን የመጠቀም ባህል የማሳደግ አላማ እንዳለው ለኢዜአ ገልጸዋል።

የሀገር ውስጥ ምርትን ከመጠቀም ባሻገር ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ ምርት በማምረት ተወዳዳሪ መሆንን ታሳቢ ያደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

የንግድ ሳምንቱ በአምራቾች እና ሸማቾች መካከል የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንዲሁም ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለማግኘት እንደሚያስችል ተናግረዋል።

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት እንዲሁም የክልል ቢሮዎች በንግድ ሳምንቱ ላይ ለማህበረሰቡ የሚሰጧቸውን አገልግሎታቸውን እንደሚያስተዋውቁም ነው የገለጹት።

200 ሺህ ሰዎች የንግድ ሳምንቱን ይጎበኙታል ተብሎ እንደሚጠበቅ በመጠቆም።

የፖሊሲ አውጪዎች፣ የንግድ ማህበረሰብ አባላት፣ ሸማቾች እና የንግድ ባለሙያዎች የሚሳተፉባቸው የፓናል ውይይቶችም ይካሄዳሉ ብለዋል።

በውይይቶቹ የወጪ ንግድ ገቢን ማሳደግ፣ የንግድ መዘመን፣ የሀገር በቀል ምርቶች ግብይት ተደራሽነት ማሳደግ፣ ተወዳዳሪነት እና ተጓዳኝ ጉዳዮች ላይ አዳዲስ የመፍትሄ ሀሳቦችም እንደሚቀርቡ አመልክተዋል።

የንግድ ሳምንቱ በጥራት መንደር መካሄዱ ከማምረት ባለፈ ለጥራት የተሰጠውን የተለየ ትኩረት የሚያሳይ ነው ብለዋል።

መንግስት ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት የሚያስችሉ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት የተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የሀገር ውስጥ ተኪ ምርትን በመጨመር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ነው የገለጹት።

የወጪ ንግድ እምርታ፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ብዛትና አይነት መጨመር እንዲሁም ወደ ህጋዊ የንግድ ስርዓት የሚገቡ ነጋዴዎች ቁጥር ማደግ ለሀገር ውስጥ ምርት እድገት የበኩሉን ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

አቶ ወንድሙ ዜጎች የኢትዮጵያን ምርት እና አገልግሎት እንዲጎበኙና እንዲሸምቱ ጥሪ አቅርበዋል።

የመጀመሪያው የኢትዮጵያን ይግዙ የንግድ ሳምንት በነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም መካሄዱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም