ከቃል ኪዳን ወደ ተግባር፤ የናይሮቢ እና አዲስ አበባ ጉባኤዎች ትስስር - ኢዜአ አማርኛ
ከቃል ኪዳን ወደ ተግባር፤ የናይሮቢ እና አዲስ አበባ ጉባኤዎች ትስስር

አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ውይይቶችና መድረኮች ላይ በጋራ ድምጿን የማሰማት አቅሟን እያሳደገች ይገኛል።
እ.አ.አ በ2023 በኬንያ ናይሮቢ የተካሄደው የመጀመሪያው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የዚሁ በአንድነት የመቆም ዋነኛ ማሳያ ነው።
በናይሮቢው ጉባኤ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ፣ የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌይን እና የዓለም ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ጨምሮ ከ30 ሺህ በላይ ተሳትፈዋል።
በጉባኤው “የናይሮቢ ድንጋጌ” በሚል 11 ነጥቦችን የያዘ የአቋም መግለጫ ወጥቷል።
የድንጋይ ከሰል በኃይል አማራጭነት የሚጠቀሙ ሀገራትና ተቋማት፣ በአቪዬሽንና የማሪታይም ትራንስፖርት ላይ ዓለም አቀፍ የካርቦን ታክስ መጣል አለበት የሚለው ጉዳይ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው።
ዓለም አቀፍ የፋይናንስ መዋቅርን በማማሻል ለአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ያለውን አቅርቦት ማሳደግ፣ የአፍሪካን የታዳሽ ኃይል አቅም እ.አ.አ በ2030 300 ጊጋ ዋት ማድረስ፣ አፋጣኝ የአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎች፣ የጉዳት ካሳ ክፍያ ፈንድ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራ የእዳ እፎይታ ማድረግ፣ የማይበገር አቅም መገንባት፣ የአፍሪካ የተፈጥሮ ሀብቶች ከአየር ንብረት ጥበቃ ጋር አጣጥሞ መጠቀም፣ ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር እንዲሁም የወጣቶችና ሴቶች አካታችነት ማሳደግ የአቋም መግለጫው ያተኮረባቸው ሌሎች ነጥቦች ናቸው።
ለጋሾች 26 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ድጋፍ ለማድረግ ቃል የገቡ ሲሆን የአፍሪካ ልማት ባንክ እ.አ.አ 2025 ማብቂያ ለአየር ንብረት ለውጥ መከላከል የሚያደርገውን የፋይናንስ ድጋፍ ወደ 23 ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ ቃል ገብቶ ነበር።
የናይሮቢው ጉባኤ ነጥቦች አፍሪካ በተሳተፈችባቸው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ መድረኮች ላይ በጋራ ድምጿን እንድታሰማ ትልቅ አቅም ፈጥሯል።
በተለይም የካርቦን ታክስ፣ የሴቶች እና ወጣቶች አካታችነት፣ የታዳሽ ኃይል ምንጮን መጨመርና ቀጣናዊ ትብብርን ማጠናከር ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኙ አስችሏል።
ይሁንና ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ፋይናንስ ቃል ኪዳኖች በሚገባ አለመፈጸም፣ የካርቦን ታክስ ሀሳቦችን ወደ ተጨባጭ የተግባር ፖሊሲ የመቀየር ፈተና፣ የእዳ እፎይታን በሚፈለገው ደረጃ አለማግኘት እና ተጋላጭ የህብረተሰብ ክፍሎች የኃይል አቅርቦት ተደራሽነት በዋናነት የሚጠቀሱ ፈተናዎች ናቸው።
ከናይሮቢው ጉባኤ በኋላ የነበሩ ስኬቶች እና ማነቆዎች በአዲስ አበባ ከጳጉሜን 3 እስከ 5 ቀን 2017 ዓ.ም የሚካሄደውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አጀንዳን የቀረጹ ናቸው።
የአዲስ አበባው ጉባኤ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ህብረት የጋራ አዘጋጅነት የሚካሄድ ነው።
ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት መፍትሄዎችን ማፋጠን፥ የአፍሪካን አረንጓዴ ልማት በፋይናንስ መደገፍ" የጉባኤው አበይት መሪ ሀሳብ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
ጉባኤው የናይሮቢ ድንጋጌን እንደ አሻራ በመጠቀም በአየር ንብረት ለውጥ ቃል የተገቡ ጉዳዮች ወደ ተግባር መቀየር ላይ ዋነኛ ትኩረቱን አድርጎ ይመክራል።
አፍሪካ በአንገብጋቢው አህጉራዊ ጉዳይ ላይ የመሪነት ሚናዋን ማሳደግ በምትችልበት ሁኔታ ላይም ምክክር ይደረጋል።
በጉባኤው በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል እና መቆጣጠር ላይ በአህጉር አቀፍ እና በሀገራት ደረጃ የተከናወኑ ስራዎች ይገመገማሉ።
ለሰው ልጆች ፈተና የሆነውን የአየር ንብረት ለውጥ መከላከልና መቋቋም የሚያስችሉ ውሳኔዎች የሚተላለፉበት ትልቅ ጉባኤ እንደሆነም እየተገለጸ ይገኛል።
ጉባኤው አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከልና ለመቋቋም በምታደርገው ጥረት ቅድሚያ የምትሰጣቸውን ጉዳዮች አቅጣጫ ለማስያዝ እንደሚረዳም ተመላክቷል።
አፍሪካ ለአየር ንብረት ብክለት የምታበረክተው አስተዋጽኦ አነስተኛ ቢሆንም በሚደርሰው ተጽዕኖ ግን ከፍተኛ ተጎጂ መሆኗን የገለጸው የአፍሪካ ህብረት ጉባኤው የአፍሪካ ሀገራት ፍትህን እንደሚጠይቁ አስታውቋል።
አፍሪካ መር የአየር ንብረት ለውጥ መፍትሄዎችም ይቀርባሉ።
የከፍተኛ ደረጃ ምክክሮች፣ የሚኒስትሮች ውይይት፣ አውደ ርዕዮች፣ የወጣት ፎረሞች እና የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ስራን የሚያሳዩ ቀጣናዊ መካነ ርዕይ(ፓቪሊዮኖች) የጉባኤው አካል ናቸው።
ኢትዮጵያ አረንጓዴ አሻራን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል እየወሰደችው ያለው እርምጃና ለአየር ንብረት ተስማሚ የሆነ አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመፍጠር እያከናወነች ያለው ስራ በጉባኤው በተሞክሮነት ታቀርባለች።
በብራዚል ቤለም በሚካሄደው 30ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ(ኮፕ 30)፣ በአሜሪካ ኒው ዮርክ በሚካሄደው 80ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፣ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ ለሚካሄደው የቡድን 20 አባል ሀገራት ጉባኤ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ሁነቶች ላይ የሚቀርቡ የአፍሪካ አጀንዳዎች እንደሚቀረጹም የአፍሪካ ህብረት መረጃ ያመለክታል።
ጉባኤው የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ራዕዮች ወደ ሚጨበጥ ውጤት የመቀየር ስራን ጠንካራ የጋራ አቋም የሚያዝበት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ መንግስት እና የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን በጉባኤው ትርጉም ያለው ውጤት እና ለውጥ የሚፈጥር ውይይት እንዲካሄድ በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ።
በጉባኤው ላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ አርሶ አደሮች፣ ተመራማሪዎች፣ የግሉ ዘርፍ፣ ዓለም አቀፍ አጋሮችና ሌሎች ተዋንያን እንደሚሳተፉ ተገልጿል።