ቀጥታ፡

በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ መካፈላችን ለሀገር ዘላቂ ሰላም ግንባታ ያለንን ሚና እንድናሳድግ አቅም እየፈጠረልን ነው - አካል ጉዳተኞች

ባሕር ዳር፤ ነሐሴ 12/2017 (ኢዜአ)፡- በሀገራዊ ምክክር ሂደት ላይ መካፈላችን ለሀገር ዘላቂ ሰላም ግንባታ ያለንን ሚና እንድናሳድግ አቅም እየፈጠረልን ነው ሲሉ አካል ጉዳተኞች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለሀገራዊ ምክክሩ እያደረገ ያለውን ዝግጅት በመደገፍ የበኩላቸውን እየተወጡ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ባለፉት ሶስት ቀናት ''የአካል ጉዳተኞች ሚና ለውጤታማ ሀገራዊ ምክክር በኢትዮጵያ'' በሚል መሪ ሀሳብ በባህር ዳር ከተማ ወጣቶችን፣ ሴቶችንና አካል ጉዳተኞችን ያሳተፈ የምክክር መድረክ አካሂዷል።


 

በምክክር ሂደቱ አካል ጉዳተኞች በስፋት እንዲሳተፉ እና ሀሳባቸው በአጀንዳነት እንዲካተት ማድረጉን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

በመድረኩ ከተሳተፉ አካል ጉዳተኞች መካከል ዝማም አቡሃይ በሰጡት አስተያየት፤ አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ምክክር ዝግጅት ላይ መካፈላቸው ለሀገር ዘላቂ ሰላም ግንባታ ያላቸውን ሚና እንዲያሳድጉ አቅም የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።


 

በሀገሪቱ የሚስተዋሉ አለመግባባቶችን ተቀራርቦ ለመፍታት ኮሚሽኑ ለምክክር እያመቻቸ ያለው ተግባር ወሳኝ በመሆኑ ለስኬታማነቱ የበኩላቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል።

ሌላው ተሳታፊ እያዩ ካሳ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞች ለሀገር ዘላቂ ሰላም ተገቢውን የውክልና አጀንዳ በማቅረብ ለምክክር ሂደት ስኬት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያደረጉ መሆኑን አስረድተዋል።


 

በሀገሪቱ የሚታዩ ችግሮችን ተነጋግሮ መፍታት የሚቻልበትን ታሪካዊ አጋጣሚ እውን ለማድረግ አካል ጉዳተኞች የበኩላቸውን ማበርከታቸውን ገልጸዋል።

አካል ጉዳተኞች በሀገራቸው ጉዳይ አጀንዳቸውን ማቅረባቸው የምክክር ኮሚሽኑን አሳታፊነትን ያረጋገጠ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው ተሳታፊ ተግነው ተሾመ ናቸው።


 

ይህም ለምክክሩ ውጤታማነት እንደሚያግዝና የድርሻቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ብሌን ገብረመድህን እንደገለጹት፤ በሀገሪቱ ለአለመግባባት ምክንያት የሆኑ ጉዳዮችን በመለየት ዘላቂነት ባለው መንገድ ተነጋግሮ መፍታት ያስፈልጋል።

ለዚህም አጀንዳዎችን የማሰባሰብ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በምክክር ሂደትም የአካል ጉዳተኞች ሀሳብ በአጀንዳነት እንዲካተት መደረጉን ጠቅሰዋል።

በመድረኩ የኮሚሽኑ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም የተለያዩ አካል ጉዳተኞች ማህበራት አመራሮችና አባላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም