አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ የመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ የቴአትር ጥበብ አዘማኞች ትውልድ አካል ነበር

አዲስ አበባ ፤ነሐሴ 12/2017 (ኢዜአ)፡-አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ የመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ ቴአትር ጥበብ አዘማኞች ትውልድ አካል እንደነበር የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ (ረ/ ፕሮፌሰር) ገለጹ፡፡

የአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ /ጋሽ ደቤ/ የቀብር ሥነ ስርዓት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ነገ ነሐሴ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዓት ይፈጸማል፡፡

ከባህልና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር እና ከሙያ ማህበራትና ከሥራ ባልደረቦቹ የተውጣጣው ቀብር አስፈፃሚ ኮሚቴ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ዋና ዳይሬክተር ባረከ ታደሰ አርቲስት ደበበ እሸቱ /ጋሽ ደቤ/ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የኪነ ጥበብ ታሪክ ታላቅ ዐሻራ ያኖረ አንጋፋ የጥበብ ሰው መሆኑን ገልጿል፡

የአንጋፋው የጥበብ ሰው አርቲስት ደበበ እሸቱ ደራሲ፣ ተርጓሚ፣ አዘጋጅ እና ተዋናይ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ባለውለታ እንደነበር አስታውሰዋል፡

የአርቲስቱ የቀብር ሥነ ስርዓት ነገ ነሐሴ 13 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰዓት በመንበረ ፀባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም ተናግረዋል፡

ከዚያ በፊት አምስት ሰዓት ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር የክብር ሽኝት እንደሚደረግለትም ገልጸዋል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ (ረ/ ፕሮፌሰር )አርቲስት ደበበ እሸቱ የመጀመሪያዎቹ የኢትዮጵያ የቴአትር ጥበብ አዘማኞች ትውልድ አካል እንደነበር ገልጸዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የቴአትር ጥበብ ታሪክ እንደ ጋሽ ተስፋዬ ገሰሰ፣ አባተ መኩሪያ፣ ወጋየሁ ንጋቱ እና አባተ መኩሪያ ያሉ አንጋፋ አርቲስቶች መካከል እንደነበሩም አስታውሰዋል፡፡

እነዚህ አንጋፋ አርቲስቶች ውጭ ሀገር ድረስ ሂደው በቀሰሙት እውቀትና ባገኙት ክህሎት የቴአትር ጥበብን ለማሳደግ የለፉ እንደነበሩ አስታውሰው፤ በህይወት የቆዩት ብቸኛው ባለውለታ ጋሽ ደበበ ብቻ ነበሩ ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ፍቅር የተጠመደ ወዳጆቿን የሚወድ ጠላቶቿን አብዝቶ የሚጠላ በስራውና በሙያው የተመሰገነ አርቲስት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አርቲስት ደበበ እሸቱ በዓለም ላይ ተዋንያን የሚፈተኑበትን የቬኑስ ነጋዴ ገጸ ባህሪ ሻይሎክን በብቃት በመተወን የማይረሳ ትዝታ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ጋሽ ደበበ የመድረክ ተዋንያን ብቻ አልነበረም ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ድንቅ የፊልም ተዋናይ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

አርቲስት ተክሌ ደስታ /ጋሽ ተክሌ/ በበኩላቸው፤ ሞት አይቀሬ ቢሆንም መልካም ስራ ሰርቶ ማለፍን የመሰለ ነገር የለም ብለዋል፡፡

አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ በሙያው የተመሰከረለት የጥበብ አስተማሪ በመሆኑ ሁሌም ልናስበው እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ተዋናይና ጋዜጠኛ ተፈሪ ዓለሙ በበኩሉ አርቲስት ደበበ እሸቱ የኢትዮጵያ ብሎም የኪነ ጥበብ ምልክት መሆኑን ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያን የኪነጥበብ ሙያ ለዓለም ያስተዋወቀ አንጋፋ የቴአትርና የሀገር ባለውለታ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ የቴአትር ባለሙያዎች ማህበር ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ለሙያው መብት መከበር ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከተ ታላቅ የጥበብ አባት እንደነበር የገለጸው ደግሞ አርቲስት ካሌብ ዋለልኝ ነው፡፡

የአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ ቤተሰብ አባል የሆነው መኮንን ደጀኔ፤ አርቲስት ደበበ እሸቱ እስከ ህልፈቱ ድረስ ጊዜውን በማንበብ የሚያሳልፍ ለወጣቶች አርአያ የሚሆን እንደነበር ገልጿል፡፡ 

ጋሽ ደቤ ለሀገሩና ለሰዎች ፍቅር ያለው የሀገር ባለውለታ እንደነበርም ተናግሯል፡፡

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም