ኢዜአ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በጋራ መሥራት የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ - ኢዜአ አማርኛ
ኢዜአ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በጋራ መሥራት የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
አሶሳ፣ነሐሴ 12/2017(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ በሚዲያ ስራ እና በስልጠና ዘርፎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ።
ስምምነቱን በአሶሳ የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ እና የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ናቸው፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ በወቅቱ እንዳሉት ክልሉ በባህል፣በቋንቋ፣ በተፈጥሮ ሀብት እምቅ አቅም ያለው በመሆኑ ትብብሩ ይህንን አቅም የበለጠ ለማስተዋወቅ ያግዛል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አንጋፋ ተቋም ነው ያሉት አቶ መለሰ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ጨምሮ በሁሉም አቅጣጫዎች ኢትዮጵያን እያስተዋወቀ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገኛ የሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በርካታ ሊተዋወቁ የሚገባቸው ሀብቶች ባለቤት መሆኑን ጠቁመው ኢዜአ የካበተ ልምድና ትልቅ አቅም ያለው ተቋም በመሆኑ ይበልጥ ተቀራርቦ ለመስራት ስምምነት ተደርጓል ብለዋል።
የክልሉ መንግስትም ተቋሙ ለሚያከናውናቸው ስራዎች አስፈላጊውን ትብብርና እገዛ የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጠዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሰይፈ ደርቤ፣ ተቋሙ ላለፉት ዓመታት በመላው ኢትዮጵያ ባሉት 38 ቅርንጫፎቹ በተለያዩ ቋንቋዎች ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ስራዎችን በስፋት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የቋንቋ፣የባህል ብዘሃነት ባለቤት ከመሆን ባሻገር የታላቁ ህዳሴ ግድብ መገኛ በመሆኑ፣ የትብብር ስምምነቱ በክልሉ የተጀመሩ ሥራዎችን ወደፊት ለማሻገር ያግዛል ብለዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም የቋንቋ ብዝሃነት ያለበት በመሆኑ በተለያዩ ቋንቋዎች ዜና እና ፕሮግራሞችን ተደራሽ በማድረግ ሀገራዊ ተልዕኮውን ለመወጣት የሚያደርገውን ጥረት የሚያግዝ በመሆኑ ከክልሉ ኮሙንኬሽን ቢሮ ጋር በጋራ ለመስራት የተደረገው ስምምነት ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ክልሉ ኢትዮጵያዊያንን ያስተሳሰረው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መገኛ በመሆኑ ትልቅ የስበት ማዕከል ስለመሆኑ አንስተው፥ በቀጣይ ኢትዮጵያን አሻጋሪ የሚያደርጉ የሚዲያ ስራዎችን ከክልሉ መንግስት ጋር በቅርበት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።