የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያዊያን የመቻል አቅም፣ የጋራ ትርክት መሰረትና ብሔራዊ አርማ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያዊያን የመቻል አቅም፣ የጋራ ትርክት መሰረትና ብሔራዊ አርማ ነው
ወላይታ ሶዶ/ቦንጋ፤ ነሐሴ 12/2017(ኢዜአ)፡-ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን የመቻል አቅም፣ የጋራ ትርክት መሰረትና ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያፀና ብሔራዊ አርማ መሆኑን ምሁራን ገለጹ።
የግድቡ መገንባት በተለይ የመንግስት የዲፕሎማሲ ጥረት ከፍታ የታየበትና የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጊዜ እውን እየሆነ መምጣቱን የሚያመላክት ስለመሆኑም ይታመናል።
በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወላይታ ሶዶ እና የቦንጋ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን የሕዳሴው ግድብ ከፕሮጀክትም በላይ ለስኬታማ የልማት ጉዞ የላቀ ሀገራዊ ትርጉም እንዳለው ገልጸዋል።
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ሄኖክ ዮናስ (ዶ/ር)፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያዊያን የመቻል አቅም፣ የጋራ ትርክት መሰረት፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን የሚያፀና ብሔራዊ አርማ መሆኑንም ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የራሷን ሀብት አልምታ ለመጠቀም ያደረገችው ጠንካራ ትግልና ውጤት መሆኑን ገልጸው፤ በዚህም የኃይል ሚዛኗን ከማሳደግ ባለፈ አህጉራዊና ቀጣናዊ ትስስሯን ለማጠናከር ያላትን ጽኑ ፍላጎት በጉልህ ያሳየችበት ነው ብለዋል።
በግድቡ ግንባታ ሂደት የመንግስት የዲፕሎማሲ ጥረትና ፕሮጀክቶችን የመፈፀም አቅም በተግባር የተረጋገጠበት መሆኑንም ሄኖክ (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በሕዳሴው ግድብ ግንባታ የውጭ ጫናዎችና የሀገር ውስጥ ፈተናዎች ቢገጥሙም ኢትዮጵያዊያን በጽናት፣ በትጋትና በቁርጠኝነት ለስኬት በማድረስ ደማቅ የታሪክ አሻራ ያኖሩበት ስለመሆኑም አንስተዋል።
በቦንጋ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግኑኝነት ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ያሬድ አያሌው፤ የሕዳሴው ግድብ ከሀገር ኩራትም ባለፈ በአፍሪካ የለውጥና የመፈፀም አቅም ተምሳሌት ተደርጎ የሚወሰድ ነው ብለዋል።
የሕዳሴው ግድብ የኢትዮጵያዊያን የሕብረ ብሔራዊ የአንድነት መገለጫ እና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራስ የመፈፀም አቅማቸውን ያሳየ የሀገር ኩራት ፕሮጀክት መሆኑንም አስረድተዋል።
በመሆኑም በሕዳሴው ግድብ የታየው የመፈፀም አቅም በቀጣይ ለሌሎች ታላላቅ የልማት ሥራዎችም መነሻ በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ለልማትና እድገት በጋራ መትጋታችንን ማጠናከር ይኖርብናል ብለዋል።